ኢትዮጵያ መድን በአብዲሳ ጀማል ብቸኛ ጎል ወልዋሎን 1ለ0 በመርታት የዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።
ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ጎል ባጠናቀቁት ኢትዮጵያ መድኖች በኩል አዲስ ተስፋዬ ፣ መስፍን ዋሼ እና አቡበከር ሳኒ ወጥተው ከቅጣት በተመለሰው ሚሊዮን ሠለሞን ፣ ከጉዳት በተመለሱላቸው ሐይደር ሸረፋ እና መሐመድ አበራ ሲተኳቸው በመቻል በተሸነፉት ወልዋሎዎች በተደረገ የሁለት ተጫዋቾች ቅያሪ ናትናኤል ዘለቀን በሠለሞን ገመቹ እና የአብስራ ሙሉጌታን በሳምሶን ጥላሁን ቦታ ቀይረው ቀርበዋል።
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሠ እየተመራ የጀመረው የሳምንቱ የመክፈቻ መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ደካማ ፉክክርን ያደረጉበት ነበር። በጨዋታው አስሩን ደቂቃዎች በመጠኑም ቢሆን ከግራ መስመር መነሳት መርጠው ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ወልዋሎዎች ጋዲሳ ከዚሁ መስመር ከቅጣት አሻምቶ በተከላካዮች ተጨራርፋ እግሩ ስር የደረሰችውን ኳስ ደካማ በሆነ ሙከራ ቡልቻ መቶ አቡበከር በቀላሉ የያዘበት ምንአልባት በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ያላየናት ብቸኛ ሙከራ ሆናለች።
ከራስ ሜዳ ከሚደረጉ የአንድ ሁለት ንክኪዎቻቸው በኋላ ረዘም ባሉ ተሻጋሪ ኳሶች መጫወትን መርጠው የታዩት መድኖች ኳስን እንደመቆጣጠራቸው ዕድሎችን ለማግኘት የሄዱበት ርቀት የተሳካ አልነበረም ይሁን እንጂ 38ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ከመስመር የተሻማን ኳስ በግንባር ገጭቶ በረከት ከያዛት አጋጣሚ ውጪ በብዙ መልኩ ደብዘዝ ያለ ፉክክርን ያየንበት እና ጥራት ያላቸው ሙከራዎች ለመመልከት ያልታደልንበት አጋማሽ ያለ ጎል ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል የሁለት ተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ የተመለሱት መድኖች በጥቂቱም ብልጫውን ሲወስዱ በአንፃሩ ወልዋሎ ረጃጅም ኳስን ተጠቅመው መጫወትን መርጠው የታዩበት ነበር። ብዙም ከመጀመሪያው አጋማሽ ያልተሻሻሉ እንቅስቃሴዎችን እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ 71ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ የቅጣት ምት ኳስ ዳዋ መቶ አቡበከር ያወጣት እንዲሁም ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ኪሩቤል ከግራ ሲያሻማ ጋዲሳ በግንባር ገጭቶ አቡበከር ያወጣበት በእንቅስቃሴ ቢበለጡም በሙከራ ረገድ ግን የተሻሉ መስለው መታየት የቻሉት ወልዋሎዎች ነበሩ።
መደበኛው ደቂቃ ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩ ወደ ሳጥን በመሳብ መንቀሳቀስን በይበልጥ መከወን የጀመሩት ኢትዮጵያ መድኖች በ80ኛው ደቂቃ በዚሁ አጨዋወት ሐይደር ሸረፋ በጥሩ ዕይታ የጣለለትን ኳስ አብዲሳ ጀማል ወደ ግብነት ለውጦ ቡድኑን ቀዳሚ ካደረገ በኋላ የቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ነገርን ሳንመለከት 1ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ድሉም ለኢትዮጵያ መድን የመጀመሪያ በአንፃሩ ወልዋሎዎች አምስተኛ ሽንፈታቸው ሆኖ ተመዝግቧል።