ሪፖርት | የአበበ ጥላሁን ብቸኛ ግን አዞዎቹን አሸናፊ አድርጋለች

ብርቱ ፉክክር በታየበት ጨዋታ አዞዎቹ ተከታታይ ድላቸውን ሲያስመዘግቡ ዐፄዎቹ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሽንፈት አስተናግደዋል።

ዐፄዎቹ ከንግድ ባንክ ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ አሰላለፍ ብሩክ አማኑኤል እና ቢኒያም ላንቃሞን በአትርሳው ተዘራ እና ቃልኪዳን ዘላለም ሲተኩ አዞዎቹ በበኩላቸው በባህር ዳር ከተማ ላይ ድል ከተቀዳጀው ቋሚ አሸናፊ ፊዳ እና እንዳልካቸው መስፍንን በአበበ ጥላሁን እና ቡታቃ ሸመና ተክተው ገብተዋል።

በሙከራዎች ባይታጀብም ጥሩ ፉክክር በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች ኳሱን ተቆጣጥረ ለመጫወት የሞከሩበት ሲሆን አርባምንጭ ከተማዎች በበኩላቸው በመልሶ ማጥቃቶች የግብ ዕድል ለመፍጠር የጣሩበት ነበር። ጨዋታው በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃም አዞዎቹ በአበበ ጥላሁን አማካኝነት መሪ መሆን ችለዋል። ተከላካዩ ካሌብ ከማዕዝን ምት አሻግሯት ተከላካዮች የመለሷትን ኳስ ከግቡ አፋፍ ላይ ሆኖ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው።

በአጋማሹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም የጠሩ የግብ ዕድሎች ያልፈጠሩት እና ይባስ ብሎ ለአዞዎቹ የመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ የነበሩት ዐፄዎቹ በሁለት አጋጣሚዎች በቃልኪዳን ዘላለም ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፤ ሆኖም ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውስጥ ማርቲን ኪዛ አሻምቷት ቃልኪዳን ዘላለም በግንባሩ ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ብርቱ እና ማራኪ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያለቀላቸው የግብ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። እንደ ቡድን በመከላከል ከኳስ ውጭ በተደራጀ መንገድ ጫና ፈጥረው በመጫወት በመልሶ ማጥቃቶች ዕድሎች ለመፍጠር የጣሩት አዞዎቹ በአሕመድ ሑሴን እና በበፍቅር ግዛው አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሁለት ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፤ በተለይም አሕመድ ሑሴን አማካዩ ቡታቃ ሸመና በረዥሙ አሻግሮለት የሐቢብ መሐመድን የትኩረት ችግር ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው የመለሰበት ኳስ የአዞዎቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ የተቃረበ ነበር።

የአዞዎቹን ጫና ተቋቁመው የተሳኩ ቅብብሎች ለማድረግ ተቸግረው የቆዩት እና በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫና መፍጠር የቻሉት ዐፄዎቹ በቃልኪዳን ዘላለም ካደረጉት ሙከራ በኋላ ዘለግ ላለ ጊዜ ሙከራ ሳያደርጉ ቆይተው በተጠቀሰው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በቢኒያም ላንቃሞ እና ናትናኤል ማስረሻ አማካኝነት ሙከራዎች አድርገዋል። ቢኒያም ላንቃሞ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አከባቢ የተገኘችውን የቆመች ኳስ በቀጥታ መቶ ፋሪስ አለዊ የመለሳት እና ቢኒያም አሻምቷት ናትናኤል ከተከላካዮች አፈትልኮ በደረቱ አሳርፎ ከመምታቱ በፊት ፋሪስ አለዊ በድንቅ ቅልጥፍና የተቆጣጠራት ኳስም ዐፄዎቹን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

የጨዋታው የመጠናቀቂያ ፊሽካ በሚጠበቅበት ቅፅበትም አዞዎቹ በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ ማግኘት ቢችሉም በሚያስቆጭ መንገድ አጋጣሚውን አምክነው ጨዋታው 1ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።