መረጃዎች | 22ኛ የጨዋታ ቀን

በስድስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የሚደረጉ ሁለት መርሐግብሮች በተከታዩ ጥንቅር ተዳስሰዋል ።

ባህር ዳር ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ያጋጠማቸውን እና አራት ድሎችን አከታትለው በድል የቋጩትን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመሩት ባህር ዳር ከተማዎች ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ያስተናገዱትን ሽንፈት በድል ለመካስ ከወቅቱ የሊጉ መሪ  ሲዳማ ቡና ጋር ብርቱ የሆነ ፉክክርን ያስተናግዳሉ። ካደረጋቸው አምስት መርሐግብሮች ሁለት ድል እና ሦስት ሽንፈቶችን በማስተናገድ በደረጃ ሰንጠረዡ ከተጋጣሚው በስድስት ነጥቦች አንሶ 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ በሦስተኛው ሳምንት መርሐግብር ወቅት ሀዲያ ሆሳዕናን በመስመር አጨዋወት 2ለ0 ረትቶ የነበረ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ግን ቡድኑ ከመስመር በሚነሳበት ጊዜ የወጥነት ችግሮች በመኖራቸው እና ለመልሶ ማጥቃት በቀላሉ ተጋላጭ ሆነው መታየታቸው በተጋጣሚው ሊሸነፉ ግድ ብሏል። በነገው ዕለት የሚገጥሙት ሲዳማ ቡናን እንደመሆኑ በይበልጥ ተጋላጭነታቸው ላይ ሽፋን ሰጥተው ማሻሻያ የማያደርጉ ከሆነ እንዲሁም ደግሞ ጠጣር የሆነውን የመከላከል አደረጃጀት ማለፍ ቀላል ስለማይሆን ግቦችን ለማግኘት መቸገሩ አይቀርም።

ከመክፈቻ መርሐግብራቸው በኋላ አንድም ነጥብ ያልጣሉት ሲዳማ ቡናዎች ነገም ካቆሙበት ድል ለመቀጠል የውጤት ርሃቡን ለማስታገስ ከሚጫወተው ባህር ዳር ከተማ ጋር ይጫወታሉ። አስራ ሁለት ነጥቦችን በመሰብሰብ የሊጉን አናት ተቆናጠው የሚገኙት ቡናማዎቹ ከጨዋታ ጨዋታ እያሳደጉ የመጡበትን ኳስን ይዞ የመጫወት ታክቲክ ሳይለውጡ እንደሚቀርቡ ከወዲሁ መናገር ይቻላል። ኳስን ከመቆጣጠር ባለፈ ሁለቱን መስመሮች በጥልቅ አጨዋወት ተጠቅሞ አንዳች ነገርን መፍጠር እንደሚችል በተከታታይ ያስመሰከረው የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቡድን ነገም ይህንኑ አቀራረብ ከፍ ባለ ደረጃ አሳድጎ እንደሚቀርብ ቢጠበቅም የሚገጥሙት ስድስት ነጥቦችን በተከታታይ ያጣውን እና ሦስት ነጥብን ለማግኘት ወደ ሜዳ የሚገባውን ባህር ዳር ከተማን በመሆኑ ጨዋታው ቀላል ላይሆን እንደሚችል በድፍረት መናገር ያሻል።

ባህር ዳርም ሆነ ሲዳማ ቡና ከጉዳት እና ቅጣት ነጻ የሆነ ስብስባቸውን ይዘው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

ተጋጣሚዎቹ እስካሁን በአስር የሊግ ጨዋታዎች ሲገናኙ ሲዳማ ቡና አምስት ባህርዳር ከተማ ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች ሲያሸንፉ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ባህር ዳር 11 ሲዳማ ቡና ደግሞ 17 ግቦች አስቆጥረዋል።

ባህርዳር ከተማ በመጨረሻዎቹ ሦስት የእርሰ በርስ ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈት ከማስመዝገቡም ባለፈ በጨዋታዎቹ ስምንት ግቦች አስተናግዷል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወላይታ ድቻ

ባለፉት ሁለት የጨዋታ ሳምንታት በተለያየ ጎዳና የተጓዙ ክለቦችን የሚያገናኘው ጨዋታ ምሽት ላይ ይደረጋል።

የፕሪሚየር ሊጉን የመጀመሪያ መርሐግብር በድል ቢጀምሩም በቀጣይ አራት ጨዋታቸው ማሸነፍ የተሳናቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከሁለት ሽንፈት እና ከአንድ የአቻ ውጤት በኋላ ሌላ ሦስት ነጥብ ፍለጋ ላይ ለመሰማራት ከጠንካራው ወላይታ ድቻ ጋር ይጫወታሉ። ዓመቱን በድል ቢጀምሩም አከታትለው ሽንፈት እያስተናገዱ የተጓዙት እና በሁለቱም የሜዳ ክፍላቸው ላይ እየተስተዋሉባቸው የሚገኙ ክፍተቶችን ማረም ዋነኛ ሥራቸው እንደሚሆን የሚጠበቁት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ግብ የማስቆጠር አቅማቸውንም ሆነ ባለፈው ዓመት አብሯቸው የነበረውን የመከላከል መዋቅር በትኩረት ማስተካከል ያሻቸዋል። አራት ነጥብን ብቻ ይዘው በደረጃ ሰንጠረዡ 16ኛ ላይ ተቀምጠው የሚገኙት ነብሮቹ ለፈጣን ሽግግር ቅድሚያውን የሚወስደው ወላይታ ድቻን እንደመግጠማቸው ለማሸነፍ ከፍ ያለ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው መናገር ይቻላል።

ከመጀመሪያው ድላቸው በኋላ በመጠነኛ መንገራገጭ ወርደው በመቅረብ ተከታታይ ሽንፈትን ለመቅመስ ተገደው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በአራተኛ ሳምንት ከመመራት ተነስተው ኢትዮጵያ ቡና ላይ ወሳኝ ድል ከተቀናጁ በኋላ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንታቸውም ስሑል ሽረ ላይ ሦስት ነጥብን ሸምተው ለሌላኛው ድል ነገ ጎረቤታቸው ሀዲያ ሆሳዕናን ያስተናግዳሉ። ከፍ ያለ የሽግግር ጨዋታን በሒደት ተጠቅመው ግብን ለማስቆጠር ጥረት የሚያደርጉት የጦና ንቦቹ ባለፉት ጨዋታዎቻቸው ላይ ያሳዩአቸው አቀራረቦች ላይ ለውጥን ሳያደርጉ እንደሚገቡ ቢጠበቅም የሚገጥሙት በወቅታዊ የውጤት ቀውስ ውስጥ ያለውን ሀዲያ ሆሳዕናን በመሆኑ ትልቅ ፈተና እንደሚያስተናግዱ መናገር ይቻላል።

ሀዲያ ሆሳዕና የጫላ ተሺታን ግልጋሎት ጨምሮ ተመስገን ብርሃኑ ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ እና አስጨናቂ ፀጋዬን በጉዳት ያጣል። ወላይታ ድቻዎች ግን ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በአስር አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም እኩል አራት አራት ጨዋታዎች ሲሸናነፉ የተቀሩ ሁለት መርሐግብሮች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።