ሪፖርት|  አዝናኝ የነበረው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ድሬዳዋ ከተማ እና አዳማ ከተማ ያገናኘው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ድሬዳዋ ከተማዎች በመጨረሻ ጨዋታቸው ሽንፈት ከገጠመው ቋሚ 11 ኢስማዒል አብዱልጋኒዩ እና ቻርለስ ሙሴጌን በድል አዲስ ገብሬ እና መስዑድ መሐመድ ተክተው ሲገቡ አዳማ ከተማዎችም በአንፃሩ ጉዳት በገጠመው ዳግም ተፈራ በናትናኤል ተፈራ ተክተው ገብተዋል።


ጥሩ ፉክክር እና ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት አዳማ ከተማዎች ደግሞ አጥቂዎቹን መሰረት ያደረጉ ቀጥተኛ ኳሶች እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር የጣሩበት ነበር። በሀያ ሦስተኛው ደቂቃም ጀሚል ያዕቆብ ከፍቅሩ አለማየሁ ጋር ታግሎ ከቀኝ መስመር ያሻማትን ኳስ መሐመድኑር ናስር በጥሩ መንገድ በመቀስ ምት አስቆጥሮ ብርቱካናማዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ሆኖም የቡድኑ መሪነት የቆየው ለሁለት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በሀያ አምስተኛው ደቂቃም ቢንያም አይተን ከመሀል ሜዳ የተሰነጠቀለትን ኳስ ግብ ጠባቂውን በማለፍ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።


ከግቦቹ በኃላም ተመሳሳይ መልክ የነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ በአቻ ውጤት የተቋጨ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ፉክክር እንዲሁም በርከት ያሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በአጋማሹ የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው አዳማዎቹ በነቢል ኑሪ ፣ አሜ መሐመድ ለግብ የቀረቡ መከራዎች አድርገዋል።

በተለይም አሜ መሐመድ ከኤልያስ ለገሰ የተቀበላትን ኳስ መቶ አብዩ ካሳሁን አድኗት ነቢል ኑሪ ከማግኘቱ በፊት ጀሚል ያዕቆብ ወደ ውጭ ያወጣት ሙከራ እጅግ ለግብ የቀረበች ነበረች።

ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም ያለቀላቸውን ሙከራዎች ለማድረግ እስከ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የቆዩት ብርቱካናማዎቹ በጨዋታው መገባደጃ በርከት ያሉ ሙከራዎች አድርገዋል። ሙኸዲን ሙሳ፣ ያሬድ ታደሰ እና አብዱሰላም የሱፍ ሞክረዋቸው ናትናኤል ተፈራ ያዳናቸው ኳሶች ይጠቀሳሉ።

እንዲሁም ተቀይሮ በመግባት ሁለት ጥሩ ሙከራዎች ያደረገው ተመስገን ደረስ ከመሐመድኑር ናስር የተቀበላትን ኳስ መቶ ተከላካዮች ተደርበው ያወጧት ኳስም የማታ ማታ ብርቱካናማዎቹን አሸናፊ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች ፤ በሙከራዎች የታጀበውና ጥሩ ፉክክር ያስመለከተው ጨዋታም አንድ ለአንድ በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።