በሊጉ ረዘም ያለ የግንኙነት ታሪክ ያላቸውን ክለቦች ባገናኘው የምሽቱ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጨረሻ ደቂቃ በተገኘች ጎል ሀዋሳ ከተማን 2ለ1 ረቷል።
ባለፈው በአዳማ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት ሀዋሳዎች ሦስት ለውጦችን አድርገው ሲቀርቡ ፍቃደስላሴ ደሳለኝ ፣ ሠለሞን ወዴሳ እና ታፈሠ ሠለሞን ወጥተው በሲሳይ ጋቾ ፣ እንየው ካሳሁን እና አብዱልባሲጥ ከማል ሲተኩ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ያለ ጎል ጨዋታቸውኔ አጠናቀው የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው አባይነህ ፌኖን በሽመክት ጉግሳ ፣ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን ደግሞ በፍቃዱ አለሙ በመተካት ቀርበዋል።
ለተመልካች ሳቢ ያልነበረው እና መቆራረጦች በተበራከቱበት የመጀመሪያው አጋማሽ ተሻጋሪ ኳሶችን የተጠቀሙት ሀዋሳ ከተማዎች 9ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል ፣ እንየው ካሳሁን ወደ ቀኝ የሳጥኑ አካባቢ የጣለለትን ኳስ እስራኤል እሸቱ በፍጥነት ወደ ግብ ውስጥ ሲያሻግር የተከላካዩ ጌታሁን ባፋ ዝንጉነት የጠቀመው ዓሊ ሱለይማን ኳሷን በመንጠቅ መረብ ላይ አሳርፏታል።
ግብ ካስተናገዱ በኃላ በፈጣን ሽግግር በቶሎ ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ለመድረስ የሞከሩት ኤሌክትሪኮች ሀዋሳዎች በመከላከሉ የሚሰራቸው ስህተቶች አግዘዋቸው አከታትለው ሙከራዎችን ማድረግ ጀምረዋል። ፍቃዱ አለሙ አከታትሎ ካደረጋቸው አደገኛ የቅጣት ምት ሙከራዎች በኋላ ቡድኑ 37ኛው ደቂቃ የአቻነት ጎልን አግኝቷል ፣ ከራሳቸው ሜዳ በረጅሙ ወደ ቀኝ የተጣለን ኳስ አቤል ሀብታሙ ከቀኝ ወደ ውስጥ መሬት ለመሬት ሲያሻግር በረከት ሳሙኤል ለማውጣት በተንሸራተተበት ወቅት በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሯት ጨዋታው 1ለ1 ሆኗል።
ከዕረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም ባልተሻሻሉ እንቅስቃሴዎች የቀጠለው የቡድኖቹ ጨዋታ መሐል ሜዳ ላይ በይበልጥ የተገደበ እንቅስቃሴን የተመለከትንበት ነበር።
ቀዝቃዛ በነበረው አጋማሹ ሀዋሳዎች ዮሴፍ እና ወንድማገኝን ኤሌክትሪኮች ደግሞ ናትናኤል እና እዮብን ወደ ሜዳ በማስገባት በአዳዲስ ጉልበት ማጥቃታቸውን ለማጠናከር ሙከራ ያደረጉ ሲሆን 80ኛው ደቂቃ ላይ በኤሌክትሪክ በኩል ተቀይሮ የገባው እዮብ ከግራ ወደ ውስጥ የሰጠውን አቤል ከግብ ጠባቂው ሰይድ ጋር ተገናኝቶ ከመከነበት አጋጣሚ በኋላ የመጨረሻዎቹን አምስት ደቂቃዎች ጫናን የፈጠሩት ኤሌክትሪኮች 89ኛው ደቂቃ ላይ ከሽመክት ጉግሳ ጋር ጥሩ አንድ ሁለት ቅብብልን ያደረገው ተቀይሮ የገባው እዮብ ገብረማርያም ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ መሪነት አሸጋግሯል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀረው ሀዋሳዎች የአቻነት ጎልን ለማግኘት ተቃርበው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻም ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።