መረጃዎች | 25ኛ የጨዋታ ቀን

የሰባተኛው ሳምንት ሁለት የመክፈቻ መርሐግብሮችን የተመለከ ጥንቅር እነሆ !

ባህር ዳር ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

በወቅታዊ አቋማቸው ጠንካራ የሆኑ ሁለት ቡድኖችን የሚያገናኘው የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

በአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው እየተመሩ በሊጉ ካደረጓቸው የስድስት ሳምንታት ጨዋታዎቻቸው በሦስቱ ድልን በሦስቱ ደግሞ ሽንፈት በማስተናገድ ከወገብ በላይ ተቀምጠው የሚገኙት ባህር ዳሮች በመጨረሻ መርሐግብራቸው መሪው ሲዳማ ቡናን 2ለ0 ከረቱበት ድላቸው ለመቀጠል ከሌላኛው ጠንካራ ቡድን ወላይታ ድቻ ጋር ይፋለማሉ። በይበልጥ ለፈጣሪ ተጫዋቾቹ ነጻነት በመስጠት መስመሮችን ለመጠቀም የሚጥረው ቡድኑ በአርባምንጭ በተሸነፈበት የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ የነበረበትን የአጨራረስ ክፍተት መድፈኑን ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ላይ ብናስተውልም ከአጨራረስ አኳያ ግን አሁንም ያለበትን ውስን ክፍተት የማያሻሻል ከሆነ የሚገጥመው ተገማች መሆን የማይችለውን ወላይታ ድቻን በመሆኑ የሚገጥመው ፈተና ቀላል አይሆንም።

በመጀመሪያ ሳምንት ኤሌክትሪክ ላይ ካስመዘገቡት ድል በኋላ በነበሩዋቸው ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት የቀመሱት የጦና ንቦቹ ያለፉትን ሦስት መርሐግብሮች ላይ ግን ለተጋጣሚያቸው አስቸጋሪ ሆነው ከመታየታቸው በተጨማሪ ዘጠኝ ነጥቦችን መሰብሰብ መቻላቸው ቡድኑ በጥሩ መሻሻሎች ላይ እንዳለ ማሳያ ነው። ከጨዋታ ጨዋታ እያዳበረ የመጣው የመልሶ ማጥቃት እና የረጃጅም ኳስ አጠቃቀም ደግሞ ለፊት ተሰላፊ ተጫዋቾቹ አመቺ እንደነበር መታዘብ የቻልን ቢሆንም ነገ ለኳስ ቁጥጥሩ ትኩረት ሰጥተው መሐል ሜዳ ላይ በቁጥር በዝተው በመስመር ለመንቀሳቀስ የሚጥሩትን ባህር ዳሮችን እንደመግጠማቸው በተለይ የመስመር የመከላከል ውስንነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ግን እሙን ነው።

ባህር ዳር ከተማም ይሁን ወላይታ ድቻ ከቅጣትም ሆነ ከጉዳት ነፃ የሆነ ስብስባቸውን ይዘው ይቀርባሉ።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ አስር ጊዜ ተገናኝተው ባህርዳር ከተማ 3 ፣ ወላይታ ድቻ አንድ ጊዜ አሸንፈው 6 ግንኙነታቸው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የጣና ሞገዶቹ 7 ፣ የጦና ንቦቹ በበኩላቸው 5 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አርባምንጭ ከተማ

ድልን አጥብቀው የሚሹት ፈረሰኞቹ አና ተከታታይ ድል ያስመዘገቡት አርባምንጭ ከተማዎች የሚያደርጉት ጨዋታ ከሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብሮች አንዱ ነው።

በፋሲል ከነማ በመሸነፍ ዓመቱን ጀምረው በመቀጠል ከድል ጋር መገናኘት የቻሉት ፈረሰኞቹ እስከ አሁን ካደረጓቸው አምስት መርሐግብሮች ውስጥ ሁለቱን በድል ሁለቱን በሽንፈት እና አንዱን በአቻ አጠናቀዋል። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ጠንካራ ፉክክርን በማድረግ አሸናፊ ሆነው ካጠናቀቁበት ጨዋታቸው አንጻር በኢትዮጵያ መድን ወረድ ብለው የታዩት በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት ፈረሰኞቹ ቡድኑ በመስመር የጥልቅ የጨዋታ መንገድ የነበረውን መልካም ጎን በነገው ጨዋታ ላይ እንደሚመልስ ቢጠበቅም ቡድኑ ቀደም ባሉ ጨዋታዎች ላይ የነበሩትን የማጥቂያ ሦስተኛው ክፍል የአጠቃቀም መልኩን ቅርፅን የማያሲዝ ከሆነ የሚገጥመው ከተከታታይ ድሎች የመጣውን አርባምንጭ ከተማን በመሆኑ መሻሻሎች እየሻተ እንደሚጫወት መናገር ይቻላል።

በውድድር ዓመቱ ሽንፈት ፣ አቻ እና በድጋሚ ሽንፈት ገጥሟቸው አራፊ ሆነው ከተመለሱ በኋላ አምስተኛ እና ስድስተኛ ሳምንት ላይ ተጋጣሚያዎቻቸውን በተመሳሳይ አንድ ለባዶ በማሸነፍ ወደ ድል ጎዳና የገቡት አርባምንጮች ተከታታይ ሦስተኛ ድላቸውን ለማግኘት ከሊጉ ባለ ታሪክ ክለብ ከሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚፋለሙ ይሆናል። ባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማን ያሸነፉበት ጨዋታን ጨምሮ በዋናነት ረጃጅም ኳሶች አልያም በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት የሚያደርገው ቡድኑም ነገም በዚሁ የጨዋታ አቀራረብ አንዳች ነገርን ለመፍጠር ወደ ሜዳ እንደሚገባ ቢታመንም ተደጋጋሚ የጨዋታ ታክቲኩ በተጋጣሚው ፈተና ሊገጥመው ስለሚችል ለውጦችን ሊያደርግ ይገባል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በረከት ወልዴ ብቸኛው በቅጣት ቡድኑን የማያገለግለው ተጫዋች ሲሆን አርባምንጭ  ከተማዎችም ሳሙኤል አስፈሪን በጉዳት አሁንም አያገኙም።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በ18 አጋጣሚዎች እርስ በእርስ የተፋለሙ ሲሆን በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ 12 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው አርባምንጭ ከተማ በአንፃሩ 2 ጊዜ ድል አድርጎ የተቀሩት አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተፈጽመዋል።