ጥሩ ፉክክር የተስናገደበት ነገር ግን በግብ ሙከራዎች መድመቅ የተሳነው የጣናው ሞገድ እና የጦና ንቦቹ የሳምንቱ የመክፈቻ መርሃግብር ያለ ጎል ተቋጭቷል።
ሲዳማ ቡናን ካሸነፈው ቡድናቸው ባህርዳር ከተማ ፀጋዬ አበራን በመሳይ አገኘሁ ፣ አቤል ማሙሽን ደግሞ በወንድወሰን በለጠ ተክተው ሲገቡ ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው ሀድያ ሆሳዕናን ካሸነፉበት ቋሚ 11 ውስጥ ቴዎድሮስ ታፈሠን በብዙአየው ሰይፉ ብቻ ለውጠው ቀርበዋል።
ተመጣጣኝ እና ጥሩ ፉክክርን ባስመለከተን በመጀመሪያው አስራ አምስት ደቂቃዎች ባህርዳር ከተማ ለኳስ ቁጥጥሩ ቅድሚያውን በመስጠት ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው በረጅም ወደፊት በሚጣሉ ኳሶችን አዘውትረው ሲጠቀሙ የታየበት ነበር።
ረጃጅም ኳሶቻቸው ለጣናው ሞገድ ተከላካዮች ሲሳይ ሲሆኑ በተደጋጋሚ ያስተዋልንባቸው ድቻዎች 15ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ ግብ አስቆጥረው ከጨዋታው ውጪ ተብላ የተሻረችባቸው አጋጣሚ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
በ45ኛው ደቂቃ ባህርዳሮች ለግብ ተቃርበው የነበረ ሲሆን ፍሬው ሠለሞን ራሱ ከማዕዘን አስጀምሮ ዳግም ያገኛትን ኳስ አክርሮ መቶ ቢኒያም ገነቱ በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቷታል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ አቀራረብ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን ቢሆንም ብዙም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያልተደረጉበት ነበር። ቴዎድሮስ ታፈሠን በሙሉቀን አዲሱ በመተካት ከረጃጅም ኳሶች በተጨማሪ መሀል ለመሀል ለመጫወት ድቻዎች ሲሞክሩ በአንፃሩ ከመስመር መነሳት ምርጫቸው አድርገው ለመጫወት የጣሩት ባህርዳርሮች ሙጂብ ቃሲምን ወደ ሜዳ በማስገባት በተወሰነ መልኩ የማጥቃት ቅርፃቸውን ለማሻሻል ቢጥሩም ጨዋታው በሙከራዎች መድመቅ ተስኖታል።
በአጋማሹ ለባህርዳር ፍሬው ሠለሞን በድቻ በኩል ደግሞ በመልሶ ማጥቃት መሳይ ሠለሞን ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ ብዙም አጋጣሚዎች ያልተፈጠሩበት ጨዋታ በመጨረሻም 0ለ0 ተቋጭቷል።