ሪፖርት | ፈረሰኞቹ ጣፋጭ ድል ተቀዳጅተዋል

ፈረሰኞቹን ከአዞዎቹ ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ አማኑኤል አረቦ በመጨረሻዎቹ ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ፈረሰኞቹ ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአምስተኛው ሳምንት ከኢትዮጵያ መድን ጋር ነጥብ ተጋርቶ ወደ እረፍት ካመራው ቋሚ አሰላለፍ አንድ ለውጥ በማድረግ አብዱልሀፍዝ ቶፊቅን በፋዓድ አብደላ ቀይሮ ሲገባ አርባምንጭ ከተማዎች በበኩላቸው በስድስተኛው ሳምንት ፋሲል ከተማን ካሸነፉበት ቋሚ አሰላለፍ ለውጥ ሳያደርጉ ገብተዋል።

ተመሳሳይ አቀራረበ በነበረው በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ቅድሚያ ለኳስ ቁጥጥር ሰጥተው ብልጫ ለመውሰድ የጣሩበት ነበር ፤ ለግብ የቀረበ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ፈረሰኞቹ ወርቃሚ አጋጣሚዎችን አግንተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

በአስራ አንደኛው ደቂቃ  ፍፁም ጥላሁን በተከላካዮች መካከል የሰነጠቀውን ፍፁም ያለቀ ኳስ አማኑኤል አረቦ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያመከናት ወርቃማ አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበረች ፤ መድረሻቸውን አማኑኤል አረቦ ያደረጉ በርከት ያሉ ኳሶች ወደ አዞዎች ግብ ክልል የደረሱ ሲሆን በሀያ ስምንተኛው ደቂቃ በመስመር በኩል የተሻገረለትን ኳስ ብቻውን ሆኖ አግኝቶ ቢመታም የአዞዎቹ ግብ ጠባቂ ፋሪስ አላዊ መልሶበታል።

አዞዎቹ በጥሩ ቅብብል ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ ባልነበረበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሰላሳ አምስተኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ ከተከለካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ አህመድ ሁሴን አግኝቶ ጠንከር ያለ ሙከራ ቢያደርግም ባህሩ ነጋሽ ያዳነባቸው ኳስ በአጋማሹ ለአዞዎቹ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲቀጥል ቡድኖቹ ልክ እንደ አንደኛው አጋማሽ የቀጠሉተበትም ነበር። ፈረሰኞቹ በአንፃራዊነት ዳግም በሙከራ ተሽለው ተገኝተዋል።

በስልሳ ስምንተኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ ሆኖ ፍፁም ጥላሁን በግሩም ሁኔታ ያደረገ ሲሆን የአርባምንጩ ግብ ጠባቂ ወደ ውጪ አውጥቶባቸዋል።

ምንም እንኳን ፈረሰኞቹ በተደጋጋሚ ወደ አዞዎቹ ግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ጥሩ የነበረውን የአዞዎቹን የተከላካይ መስመር አልፎ ለማስቆጠር ተቸግረው ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አምርቷል። በመጨረሻዎቹ በአስር ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው በመጫወት የጥረታቸው ውጤት የሆነችዋን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል።


በሰማንያ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ወደ ግብ ተሻምቶ አማኑኤል አረቦ በግንባሩ ገጭቶ ሙከራ ሲያደርግ ግብ ጠባቂው ተፍቶት በድጋሚ እራሱ አማኑኤል ኤርቦ አግኝቶ ከመረብ ጋር አገናኝቷታል።

በቀሩት ደቂቃዎች አዞዎቹ ነጥብ ተጋርተው መውጣት የሚችሉበትን ሙከራ ቢያደርጉም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮችና ባህሩ ነጋሽ ተረባርበው አውጥቶባቸው ጨዋታው ተጠናቋል።