ከዕረፍት መልስ በተቆጠሩ ጎሎች መቻሎች 2ለ0 በሆነ ውጤት አዳማ ከተማን በማሸነፍ ተከታታይ ሦስተኛ ድል አስመዝግበው የሊጉ መሪ ሆነዋል።
መቻሎች ከንግድ ባንኩ ድላቸው ዮሐንስ መንግስቱን በአቤል ነጋሽ ከድሬዳዋ ጋር አቻ የተለያዩት አዳማዎች በበኩላቸው ምንም የተጫዋች ቅያሪን ሳያደርጉ ለጨዋታው ቀርበዋል።
10፡00 ሲል በዋና ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በፈጣን ሽግግር የበላይነቱን ገና በጊዜ የያዙት መቻሎች ፍሪምንፖንግ ከራሱ ሜዳ በረጅሙ ወደ መስመር የጣለለትን ኳስ በረከት ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ ውስጥ ባሻገራት እና ምንይሉ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት ባመለጠችው አጋጣሚ ወደ ግብ መቅረብ ጀምረዋል።
በሦስቱም የማጥቂያ ቦታዎች ላይ በሚያደርጓቸው ንክኪዎች ብልጫን ወስደው የተንቀሳቀሱት መቻሎች መሐል ለመሐል እና ከመስመር በጥልቅ የጨዋታ መንገድ በድግግሞሽ ሲያጠቁ ይስተዋል እንጂ ለመከላከሉ ጥብቅ የነበረውን የአዳማ የኋላ ክፍል መሻገሩ ላይ ተቸግረው ታይተዋል።
በ23ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ከቀኝ በኩል አቤል ነጋሽ ወደ ሳጥን ጠጋ ብሎ መትቶ ናትናኤል ተፈራ ያወጣበት እና ምንይሉ ወንድሙ ከቅጣት ያደረጋትን ሙከራ ናትናኤል አሁንም በቀላሉ የተቆጣጠራት በጨዋታው የነበሩ ደካማ ሙከራዎች ነበሩ። መቻሎች በኳስ ቁጥጥሩ አዳማ ደግሞ በመከላከሉ የተሻለ ቆይታን ያደረጉበት የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ጎል ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ምንይሉ እና አቤልን በአብዱ ሙታላቡ እና ጳውሎስ መርጊያ በመተካት ከቆሙበት የእንቅስቃሴ ብልጫቸው የቀጠሉት መቻሎች በ48ኛው ደቂቃ ከቀኝ ዳዊት ባሻገረው እና አብዱ በግንባር ገጭቶ ናትናኤል የመለሳት እና በድጋሚ ጳውሎስ ያገኛትን መልካም አጋጣሚ በግቡ ቋሚ ብረት የተመለሠችባቸው ቡድኑ በአጋማሹ በማጥቃት መሻሻሎች መግባቱን ማሳያዎች ነበሩ።
55ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ መሐል ለመሐል የሰነጠቃትን ኳስ ወደ ሳጥን ነድቶ የገባው አብዱ አክርሮ መቶ በግብ ጠባቂው ናትናኤል ኳሷ ስትመለስ ከጀርባ የነበረው ጳውሎስ መርጊያ ደርሶ ወደ ግብነት በመቀየር መቻልን መሪ አድርጓል። ወረድ ብለው ከሚከላከሉበት አጨዋወት ጎልን ካስተናገዱ በኋላ በሽግግር የተጫወቱት አዳማዎች በ70ኛው ደቂቃ ቢኒያም የፈጠረለትን ግልፅ የማግባት ዕድል ሙሴ ኪሮስ አግኝቶ አሊዮንዚ ናፊያን መክቶበታል።
በመልሶ ማጥቃት 74ኛው ደቂቃ ላይ ወደ አዳማ ሜዳ ያመሩት መቻሎች አማኑኤል ዮሐንስ በተከላካዮች መሐል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ በረከት ደስታ እየነዳ ገብቶ በድንቅ አጨራረስ ኳሷን በማስቆጠር የመቻልን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጓል። በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች አብዲ ዋበላ በአዳማ በኩል አደገኛ ሙከራን አድርጎ አሊዮንዚ ናፊያን ከመለሰበት በኋላ የቀሩት ደቂቃዎች ጎልን ሳያስመለክቱን ጨዋታው በመቻል 2ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል። ድሉም መቻልን በ13 ነጥቦች በግብ ልዩነት ከወላይታ ድቻ በልጦ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ አስቀምጦታል።