መረጃዎች | 27ኛ የጨዋታ ቀን

በ7ኛው ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን የሚከናወኑ መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ፋሲል ከነማ  ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ዐፄዎቹ ከሽንፈት ለማገገም ኤሌክትሪክ ደግሞ ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን ለማሳካት የሚፋለሙበት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

በመጨረሻው መርሐግብር በአርባ ምንጭ ከተማ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈታቸው ያስተናገዱት ዐፄዎቹ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻሉም። በነገው ዕለትም ከሽንፈት አገግመው ዳግም ከሦስት ነጥብ ጋር ለመታረቅ ለአምስት ጨዋታዎች ሳይሸነፉ ከዘለቁት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጋር ይፋለማሉ።

ዐፄዎቹ ምንም እንኳን ተከታታይ የአቻ ውጤቶች እንዲሁም አንድ ሽንፈት በማስመዝገብ ከድል ጋር ቢራራቁም በኳስ ቁጥጥር ረገድ አሁንም የተሻሉ መሆናቸው እያሳዩ ይገኛሉ። ሆኖም ኳስ እና መረብ ማገናኘት የቡድኑ ዋነኛ ድክመት ነው። ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን ካሸነፈበት የመጀመርያ ጨዋታ በኋላ ባከናወናቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ማስቆጠሩም የዚህ ማሳያ ነው። በነገው ዕለትም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን እንደመግጠማቸው ፈተናው ከባድ መሆኑ እርግጥ ነው።

ከወላይታ ድቻው የመጀመርያ ሽንፈት ወዲህ ጉልህ መሻሻል በማሳየት አምስት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች ያስመዘገቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በሀዋሳ ከተማ ላይ ከተቀዳጁት ጣፋጭ ድል መልስ ተከታታይ ሦስት ነጥብ ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታው ቡድን በቅርብ ሳምንታት የመከላከል አደረጃጀቱን ይበልጥ በማጠንከር የሚያስተናግዳቸውን ግቦች ቀንሷል። ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ግቡን ካለማስደፈሩ በተጨማሪ ያስተናገደው የግብ መጠን አንድ መሆኑም የኋላ ክፍሉን ጥንካሬ ማሳያ ነው። ሆኖም በቡድኑ የሚታየው የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ውስንነት የፊት መስመሩን ጥንካሬ ቀንሶታል።

ቡድኑ በነገው ዕለት ባለፉት ጨዋታዎች ለመልሶ ማጥቃቶች ይበልጥ ተጋላጭ የነበረው ፋሲል ከነማን መግጠሙን ተከትሎ በፊት መስመር የሚገጥመው ፈተና ከባለፉት ጨዋታዎች በአንጻራዊነት የተሻለ ነው ተብሎም ይገመታል።

በዐፄዎቹ በኩል ከሰባት ወራቶች ጉዳት የተመለሰው አማኑኤል ገብረሚካኤል ልምምድ ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ አይደርስም፤ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ግን በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ሰባት ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ አራት ጊዜ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። በጎል ረገድ ሁለቱም ቡድኖች በእኩል 9 ግቦች አስቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ስሑል ሽረ

በአንድ ነጥብ የሚበላለጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች መልስ መቐለ 70 እንደርታን በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ቡናማዎቹ የውድድር ዓመቱ ሦስተኛ ድላቸውን ለማስመዝገብ ስሑል ሽረን ይገጥማሉ። መቐለን ባሸነፉበት ጨዋታ በአንጻራዊነት የተሻሻለ ብቃት ያሳየው ቡድኑ በሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ካስተናገደ ወዲህ በመጨረሻው መርሐግብር መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። በተለይም ሽንፈት ባስተናገዱባቸው ሁለት መርሐግብሮች እጅግ የተጋለጠ የመከላከል አደረጃጀት የነበራቸው ቡናማዎቹ የባለፈውን ጨዋታ የመከላከል ጥንካሬ ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።

ቡድኑ ከተጋጣሚው አሁናዊ የማጥቃት ጥንካሬ አንፃር ብርቱ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ ባይገመትም ለጠጣሩ የስሑል ሽረ የመከላከል አደረጃጀት የሚመጥን አቀራረብ ይዞ መግባት ግድ ይለዋል።

በአምስተኛው ሳምንት በወላይታ ድቻ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈታቸውን ያስተናገዱት ስሑል ሽረዎች ከአንድ የጨዋታ ሳምንት እረፍት በኋላ ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማሉ። አምስት ግቦች አስቆጥሮ በተመሳሳይ አምስት ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ የመከላከል አደረጃጀቱ ዋነኛ ጠንካራ ጎኑ ነው። ሆኖም አዳማ ከተማን ባሸነፉበት የሊጉ የመጀመርያ መርሐግብር ላይ በጨዋታ ሦስት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ ባለፉት አራት ጨዋታዎች በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ኳስ እና መረብ ማገናኘት የቻለው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ውስን መቀዛቀዞች ተስተውለዋል።

በተለያዩ ጉዳቶች ምክንያት ተለዋዋጭ የፊት መስመር ጥምረቶች ለመጠቀም የተገደዱት አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በጥሩ መነቃቃት ዓመቱን ጀምሮ በሂደት የውጤታማነት ደረጃውን ያሽቆለቆለውን የማጥቃት አጨዋወታቸው ውጤታማነት ከፍ የማድረግ የቤት ሥራም ይጠብቃቸዋል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል በፍቃዱ ዓለማየሁ እና መላኩ አየለ ከጉዳት ባለማገገማቸው የነገው ጨዋታም ያልፋቸዋል፤ በስሑል ሽረ በኩል ደግሞ ጉዳት ላይ ከቆዩት ኬቨን አርጉዲ እና ዐወት በሪሁ
በተጨማሪ ክፍሎም ገብረሕይወት በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሰለፍም።

ከተሰረዙት የ2012 ዓ.ም ሁለት ጨዋታዎች ውጭ ሁለት ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈዋል፤ ጨዋታዎቹም በ1-0 ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።