ሁለቱ አሰልጣኞች በጋራ ወልዋሎን በዛሬው ጨዋታ እንዲመሩ ይጠበቃል።
ከቀናት በፊት ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር የተለያዩት ወልዋሎዎች አዲስ አሰልጣኝ ከመቅጠራቸው በፊት ዛሬ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ በረዳት አሰልጣኞቻቸው እየተመሩ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ቡድኑን እየመሩ ወደ ሜዳ የሚገቡት ደግሞ ከ2005 ጀምሮ በታዳጊ ቡድን እና በዋናው ቡድን በምክትል እንዲሁም በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ቡድኑን ያገለገለው ወጣቱ አሰልጣኝ ሀፍቶም ኪሮስ እና አታኽልቲ በርኸ ናቸው።
ከዚህ ቀደም በ2008 ከአሰልጣኝ እንድርያስ ብርሃኑ፣ በ2010 ደግሞ ከአሰልጣኝ ብርሃነ ገብረእግዚአብሔር መለያየት በኋላ ቡድኑን በጊዜያዊነት የመራው ሀፍቶም ኪሮስ ዳግም ጊዝያዊ አሰልጣኝ ሆኖ ቡድኑን ይመራል።
ሌላው ቡድኑን በጊዜያዊነት የሚመራው ደግሞ በ2004 ወልዋሎ ወደ ብሄራዊ ሊግ ሲያድግ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የመራው እና ላለፉት ዓመታት የከፍተኛ ሊጉን ሶሎዳ ዓድዋ በማሰልጠን የቆየው አታኽልቲ በርኸ ነው።
የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ረዳቶች ሆነው በመስራት የቆዩት ሁለቱ አሰልጣኞች ላለፉት ሁለት ቀናት ቡድኑን ልምምድ በማሰራት ላይ ከቆዩ በኋላ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ፍለጋ ንግድ ባንክን ይገጥማሉ።