ሪፖርት | ነብሮቹ ወሳኝ ድል ተጎናፅፈዋል

ሀዲያ ሆሳዕና ድሬዳዋ ከተማን በሰመረ ሀፍተይ ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል።

ድሬዳዋ ከተማዎች በስድስተኛው የጨዋታ ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ቋሚያቸው ሁለት ለውጥ በማድረግ ድልአዲስ ገብሬን እና አቤል አሰበን በማሳረፍ ኢስማኤል አብዱልጋኒዩን እና ቻርልስ ሙሴጌን ቀይረው ሲገቡ ሀዲያ ሆሳዕና በስድስተኛው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ሸንፈት ካስተናገዱበት ቋሚያቸው ሶስት ለውጥ በማድረግ ሄኖክ አርፍጮ ፣ በየነ ባንጃ ፣ ኢዮብ ዓለማየሁን አስወጥተው ኩሊባሊ ካድር ፣ ሰመረ ሀፍተይ እና ደስታ ዋሚሾን ይዘው ገብተዋል።

ጨዋታውን የመጀመር ዕድል ያገኙት ብርቱካናማዎቹ የተሳካ የኳስ ቅብብል በማድረግ በንክኪ ብልጫ ወስደው በፈጣን ሽግግር ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ግብ ክልል ለመድረስ ጥረዋል። ፍፁም የጨዋታ በላይነት ያገኙት ብርቱካናማዎቹ የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጠንካራ ሆኖ የቀረበውን የነብሮቹን ተከላካይ መስመር አልፎ ግብ ለማስቆጠር ተስኗቸዋል። ነብሮቹ በአንፃሩ በጨዋታ ቢበለጡም ግባቸውን ላለማስደፈር በጥንቃቄ ወደፊት ከመግፋት ተቆጥበው ኳሶችን በማበላሸት እየተጫወቱ የአጋማሹ ደቂቃዎች እየገፉ ሄደዋል።

የኳስ ንክኪ የበላይነት የነበራቸው ብርቱካናማዎቹ በአጫጭር ኳሶች ከመጀመሪያው ሜዳ ክፍል እስከ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል እየደረሱ ኳስ ቢያንሸራሽሩም እምብዛም ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ አጋማሹ ወደ መገባደጃ ሲደርስ በ40ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ጀምረው ያስቆጠሩት ግብ ከጨዋታ ውጪ የተባለባቸው አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበር። አጋማሹም ያለ ግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ሲመለስ ብርቱካናማዎቹ ልክ እንደ መጀመሪያው በአጫጭር ኳስ ቅብብል ነብሮቹ ደግሞ የአጨዋወት ስልታቸውን ቀይረው በረጃጅም ኳስ ወደ ፊት ኳሶችን በመጣል ተመልሰዋል። ነብሮቹ የረጃጅም ኳሶች ውጤት የሆነችዋን ግብ መረብ ላይም አክለዋል። በ48ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ሰመረ ሀፍተይ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ መትቶ ከመረብ ጋር አገናኝቷታል። በ52ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ የቆመ ኳስ ተሻምቶ በግንባራቸው ገጭተው ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ ተብሎባቸዋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ የበለጠ በሙከራዎች ደምቆ በቀጠለው በአጋማሹ ብርቱካናማዎቹ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ወደፊት ገፍተው በመሄድ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ነብሮቹም በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ የማግባት እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል። ነብሮቹ በ69ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር በኩል የተሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ኢዮብ አለማየሁ ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር። ድሬዳዋ ከተማም በተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረገ ሲሆን ምናልባትም አቻ ለመሆን የቀረቡበትን ሙከራ 75ኛው ደቂቃ ላይ አድርገው ነብሮቹ ተረባርበው ኳሱን አርቀዋል።

የድሬዎች ጫና የበረቱበት የመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች አጓጊ ሆነው ሲቀጥሉ የነብሮቹ አልሸነፍ ባይነት የገዘፈበት እና ጫናዎቹን ተቋቁመው ነጥባቸውን ይዘው ለመውጣት ከኋላ ዘግተው ጥሩ መከላከል ያሳዩበት ነበር። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩት የሀዲያ ሆሳዕናው ደስታ ዋሚሾ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ በቀይ ካርድ ተሰናብቷል። ጨዋታውም ለውጥ ሳይታይበት በሰመረ ሀፍታይ ብቸኛ ግብ ለሀዲያ ሆሳዕናዎች ሦስት ነጥብ በማጎናፀፍ ተቋጭቷል።