ወደ ግብፁ ክለብ እስማኤሊያ የሚያደርገው ዝውውር ያልተሳካለት ቢንያምን ፍቅሬ ዳግም ወደ ሊጉ የተመለሰበትን ክለብ አግኝቷል።
የቀድሞ ወላይታ ድቻ የታዳጊ ቡድን ፍሬ በመሆን እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ያለፉትን ዓመታት መጫወት የቻለው አጥቂው ቢኒያም ፍቅሬ ከግብፁ ክለብ እስማኤሊያ ጋር ለመጫወት ያደረገው ስምምነት አለመሳካቱን ተከትሎ ወደ ሀገሩ መመለሱን ከዚህ ቀደም መዘገባችን አይዘነጋም።
ወደ ሀገር ቤት መመለሱን ያወቁ የተለያዩ የሊጉ ክለቦች ሲያነጋግሩት ቢቆዩም በስተመጨረሻም ማረፊያው ቅዱስ ጊዮርጊስ መሆኑ እርግጥ የሆነ ይመስላል። ተጫዋቹ እና ክለቡ በአብዛኛው ድርድሮች ከስምምነት መድረሳቸው የታወቀ ሲሆን እጅግ በቅርቡ ፊርማውን ለክለቡ እንደሚያኖር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ፈረሰኞቹ በያዝነው የውድድር ዓመት ከስድስት ጨዋታዎች 10 ነጥብ በመያዝ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ቡድኑ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ማጣቱን ተከትሎ ቢንያም ፍቅሬ ሁነኛ ተተኪ በመሆን ቡድኑን የማጥቃት አቅም ከፍ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።