ምሽት የሚደረገው የባንክ ጨዋታ በሀገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ ይተላለፋል

በአፍሪካ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ሀገራችንን እና ምስራቅ አፍሪካን የወከለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምሽት 2 ሰዓት የሚያደርገውን ጨዋታ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ እንደሚያስተላልፍ ታውቋል።

በስምንት የአህጉራችን እንስት ክለቦች መካከል የሚደረገው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር በትናንትናው ዕለት ጅማሮውን ያደረገ ሲሆን በምድብ አንድ የሚገኙት ቲፒ ማዜምቤ እና ኤስ ፋር ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ምድባቸውን መምራት ጀምረዋል። ምድብ ሁለት ዛሬ ሲቀጥል የሀገራችን ክለብ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚገኝበት ምድብ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከ ኤፍ ሲ ማሳር እንዲሁም ንግድ ባንክ ከኢዶ ኩዊንስ (ናይጄሪያ) ጋር ፍልሚያቸውን ያከናውናሉ።

ያለፉትን ጊዜያት አህጉራዊ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን ለስፖርት ቤተሰቡ በቀጥታ እያስተላለፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይህንን የካፍ ውድድር የማስተላለፍ መብት ካላቸው 9 ግዙፍ ተቋማት መካከል አንዱ ሲሆን የሀገራችን ክለብ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርገውን ጨዋታም በመዝናኛ ቻነል አማራጩ ለአድማጭ ተመልካቾች ለማድረስ ዝግጅቱን መጨረሱን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ዛሬ ምሽት 2 ሰዓት በሞሮኮ ካዛብላንካ የሚደረገውን ጨዋታም የቅድመ ጨዋታ ትንተናን ጨምሮ ከምሽት 1 ሰዓት አንስቶ የቀጥታ ስርጭት እንደሚኖር ታውቋል።