በትልቁ አህጉራዊ መድረክ የመጀመሪያ ተሳትፏቸውን እያደረጉ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በምድብ የመጀመሪያ ጨዋታቸው በናይጄሪያ ተወካዮቹ ኤዶ ኩዊንሶች የ3-0 ሽንፈት አስተናግደዋል።
በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ጅማሬውን ባደረገው ጨዋታ ግብ የተስተናገደበት ገና በማለዳ ነበር ፤ በ5ኛው ደቂቃ ንግድ ባንኮች ኳሷን ከግብ ክልላቸው ለማራቅ ባደረጉት ሂደት ኢዶ ኩዊንሶች ያገኙትን እና ወደ ቀኝ መስመር ያወጧትን ኳስ ፎላሻዴ ኢጃሚሊሲ ወደ ሳጥን ስታሻማ ኢማም ኤሴን በግሩም አጨራረስ ቡድኗን ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጥራለች።
ግብ ካስተናገዱ በኋላ በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት የሞከሩት ንግድ ባንኮች በደቂቃዎች ልዩነት ሰናይት ቦጋለ ወደ ሳጥን ያሻማችውን ኳስ ረድዔት አስረሳኸኝ በግንባሯ በመግጨት ያደረገችው ሙከራ ለጥቂት በግቡ አግዳሚ በኩል ወደ ውጭ ወጥታባቸዋለች።
ጨዋታውን በተቻለ የራስ መተማመን መከወናቸውን የቀጠሉት ኢዶ ኩዊንሶች አከታትለው በኢሜም ኤስየን እና ኮርዴልያ ኦዶማ አማካኝነት አከታትለው ያለቀላቸው አደገኛ ሙከራዎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል።
በሂደት እየተቀዛቀዘ በመጣው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መሃል ሜዳ ላይ የተገደቡ እንቅስቃሴዎች ተበራክተው የተመለከትንበት ነበር ነገር ግን አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ የኢዶ ኩዊንሷ የግራ መስመር ተከላካይ የሆነችው ሚራክል ኡሳኒ ወደ ሳጥን ያሻማችውን ኳስ አቅጣጫውን ቀይሮ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል ወደ ውጭ የወጣችባት ኳስ እንዲሁም ኢስተር ሞሰስ ከታሪኳ በርገና ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ ሳትጠቀምባት የቀረችው ኳስ የአጋማሹ የመጨረሻዎቹ ሙከራዎች ነበረች።
ከዕረፍት መልስ ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ኤዶ ኩዊንሶች በ54ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የቅብብል ሂደት ንግድ ባንክ ሳጥን ያደረሱትን ኳስ ፎላሼድ ኢጃሚሉሲ አስቆጥሯ የቡድኗን መሪነት ማሳደግ ችላለች።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ በኋላ መሃል ሜዳ ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመመለስ ሰናይት ቦጋለን አስወጥተው ባለልምዷን ብርቱካን ገ/ክርስቶስን በመተካት ያስገቡ ሲሆን በዚህም በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻሉ ለመሆን ጥረቶችን ቢያሳዩም ይህን ጥረት ወደ ግብ ዕድሎች መቀየር ግን ሳይችሉ ቀርተዋል።
80ኛው ደቂቃ ላይ ከደቂቃዎች በፊት በኤዶ ኩዊንሶች በኩል ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው ቹክዋማካ ኦሲግዌ ከኤስተር ሞሰስ የደረሳትን ኳስ ተጠቅማ በግሩም ሁኔታ የቡድኗን ሦስተኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች።
ንግድ ባንኮች ሦስተኛ ግብ ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ተጨማሪ ግቦችን ላለማስተናገድ በተለያዩ መንገዶች የጨዋታውን ሂደት ለማዘግየት ጥረቶችን ሲያደርጉ ያስተዋልን ቢሆንም በ94ኛው ደቂቃ ግን ተቀይራ የገባችው ሜሪማጋድለን አንጆር ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ያደረገችው ሙከራ የግቡን የላይኛውን ቋሚ ለትማ ወደ መሬት ስትመለስ ኳሷ መስመር አልፋለች በሚል የመሃል ዳኛዋ ግቡን አፅድቃ የነበረች ቢሆንም በምስል በታገዘ ዳኝነት በምልሰት ታይቶ ኳሷ አላለፈችም በሚል የመሀል ዳኛዋ ውሳኔ መቀልበሱን ተከትሎ ጨዋታው በኤዶ ኩዊንሶች የ3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።