የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በተለያዩ ሀገራት ሲደረጉ አራት የሀገራችን ዳኞች ተጠባቂውን ጨዋታ እንዲመሩ መመደባቸው ታውቋል።
በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ወደ ፍፃሜያቸው የተጠጉ ሲሆን የምድብ 5ኛ እና 6ኛ ጨዋታዎችም ከቀናት በኋላ ያከናውናሉ። ታዲያ ጫናዎች እየተጠናከሩ በመጡበት በዚህ ሰዓት የውድድሩ የበላይ አካል ዳኝነት ምደባ ላይ ክፍተቶች እንዳይኖሩ እየሰራ መሆኑን ተሰምቷል።
በተለያዩ ምድቦች ተከፋፍለው ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል በምድብ 3 ከግብፅ እና ኬፕ ቨርድ ጋር ተደልድለው የሚገኙት ቦትስዋና እና ሞሪታኒያ የምድኑ 2ኛ ሆኖ ለማለፍ የሚያደርጉትን ወሳኝ ጨዋታም ኢትዮጵያዊ አልቢትሮች እንዲመሩት ምደባ ተደርጓል።
በዚህም ቦትስዋና ላይ የሚደረገውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል አልቢትር ባምላክ ተሰማ ከረዳቶቹ ተመስገን ሳሙኤል፣ ሙስጠፋ መኪ እና አሸብር ሰቦቃ ጋር እንደሚመሩት ተገልጿል።
በምድቡ ከግብፅ ቀጥሎ ኬብ ቨርድ፣ ቦትስዋና እና ሞሪታኒያ እኩል አራት ነጥቦች ይዘው በግብ ክፍያ ብቻ ተበላልጠው ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ደረጃን በመያዝ ተቀምጠዋል።