በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ሀገራችን ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ የሚያደርጉትን ጨዋታ የሚዳኙ አልቢትሮች ተለይተዋል።
በ2025 በሚደረገው የአህጉራችን ትልቁ የውድድር መድረክ ለመሳተፍ የተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያከናወኑ የሚገኝ ሲሆን የምድብ 5ኛ ጨዋታቸውንም ከቀናት በኋላ የሚከውኑ ይሆናል።
እስካሁን በተደረጉ የምድቡ አራት ጨዋታዎች አንድም ድል ማስመዝገብ ያልቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብቸኛ ነጥብ ካገኘበት የታንዛኒያ አቻው ጋር የፊታችን ቅዳሜ በኬንሻሳ ፍልሚያውን የሚያደርግ ሲሆን ይህንንም ጨዋታ ደቡብ ሱዳናዊ አልቢትሮች እንደሚመሩት ተረጋግጧል።
ሪንግ ኒየር አኬች ማሎንግ ጨዋታውን በመሐል አልቢትርነት ሲመሩት ሮበርት ዱዉኪ ሮበርት ሄነሪ እና ጋሲም ማዲር ዴሂያ በረዳትነት እንዲሁም አንቶኒ ኪሪ ኢማኑኤል ዳውድ በአራተኛ ዳኝነት ተሳትፎ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።