በአሁኑ ወቅት የመጨረሻ ልምምዱን እያደረገ በሚገኘው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ሦስት ተጫዋቾች ልምምድ አልሠሩም።
የፊታችን ሕዳር 7 እና 10 ላሉበት ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የምድብ ጨዋታዎች ዝግጅቱን ከጀመረ ሰባተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ሦስት ተጫዋቾች ልምምድ እየሠሩ እንዳልሆነ መመልከት ችለናል። ብሔራዊ ቡድኑ በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምድ እየሠራ ባለበት ሰዓት ተከላካዩ ፍሬዘር ካሳ፣ አጥቂዎቹ ቢኒያም ዐይተን እና በረከት ደስታ በጉዳት ምክንያት ልምምድ እየሠሩ አይገኝም።
አጥቂው በረከት ደስታ የውስጥ ህመም እንደሆነ እና የጉዳቱ መጠን ብዙም አሳሳቢ እንዳልሆነ ፤ ተከላካዩ ፍሬዘር ካሳ ከጉልበቱ ስር መጠነኛ ሕመም እንደተሰማው እና ሕመሙ እንዳይባባስ በመፍራት ዛሬ ልምምድ እንዳይሠራ መደረጉን እንዲሁም ሌላኛው አጥቂ ቢኒያም ዐይተን የቁርጭምጭሚት ጉዳት ያጋጠመው ሲሆን ትንሽ የቢኒያም ሕመም ጠንከር ያለ እንደሆነ እና የመሄድ ያለመሄዱን ነገር የሕክምና ቡድኑ በቀጣዮቹ ሰዓታት የሚወስን መሆኑን ፊዚዮቴራፒስት ብሩክ ደበበ ነግረውናል።
ብሔራዊ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ልምምዱን በአዲስ አበባ ስታዲየም እየሠራ የሚገኝ ሲሆን ሌሎች ተያያዥ መረጃዎች ካሉ ወደ እናንተ የምናደርስ ይሆናል።