ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዷል

በሞሮኮ እየተደረገ በሚገኘው የካፍ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ እየተሳተፉ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሁለተኛ ጨዋታቸውን አድርገው 4ለ0 በሆነ ውጤት ተረተዋል።

በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ በናይጄሪያው ኤዶ ኪዊንስ ሽንፈት አስናግዶ ከነበረው ስብሰባቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ታሪኳ በርገና ፣ ናርዶስ ጌትነት እና ሰናይት ቦጋለ ወጥተው አበባ አጄቦ ፣ ድርሻዬ መንዛ እና ሒሩት ተስፋዬ ተተክተው ገብተዋል።

በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ውስጥ የማጥቃት ደመ ነብስ ያልነበረው እና መሐል ሜዳ ላይ ብቻ ያመዘኑ እንቅስቃሴዎች በይበልጥ ያስተዋልንበት ቢሆንም በሂደት ግን በመስመሮች በኩል ፈጣን ሽግግሮችን መጠቀም የጀመሩት ሰንዳውንሶች የንግድ ባንክን የመከላከል ድክመት በመጠቀም ጎል አስቆጥረዋል። 16ኛው ደቂቃ የድርሻዬ መንዛን የቦታ ሽፋን ስህተት የተጠቀመችው ሊቦአንግ ከቀኝ ወደ ውስጥ ሰብራ ገብታ የሰጠችውን ኳስ ኖን ሀላህላ ከጀርባዋ ለተገኘችው ሜሊንዳ ክጋዲቴ አቀብላ ወደ ጎልነት ለውጣ ቡድኗን መሪ አድርጋለች።

መከላከላቸው በተጋጣሚያቸው የጫና አጨዋወት ውስጥ የወደቀባቸው ንግድ ባንኮች 26ኛው ደቂቃ በተከላካዮች ኳስን የማራቅ ስህተት የተነሳ ቦይቱሜሎ ራባሌ ሁለተኛ ጎል አክላለች። ከፉክክር አንፃር ወረድ ያሉ አቀራረቦች ነገር ግን በአመዛኙ የደቡብ አፍሪካው ቡድን ፍፁማዊ ብልጫ እየታየ የቀጠለው ጨዋታ 30ኛው ደቂቃ ላይም ግብን አስመልክቶናል።

ከቅጣት ሊቮሀንግ ያሻማችውን ኳስ ሜሊንዳ ክጋዲቴ በግንባር ገጭታ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ሦስተኛዋን ጎል ስታስቆጥር ሊሎና ዳዊቲ በበኩሏ ከሰባት ደቂቃ በኋላ አራተኛዋን ጎል ከመረብ አዋህዳለች። አምስተኛ ጎልን አስተናግደው ከጨዋታ ውጪ ተብላ ከተሻረች በኋላ ንግድ ባንኮች 43ኛው ደቂቃ ላይ ድርሻዬ ፣ አበባ እና ሒሩትን በማስወጣት በሰናይት ፣ ናርዶስ እና ታሪኳ ለውጠው አጋማሹም 4ለ0 ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት ዳግም የተመለሰው ጨዋታ ከመጀመሪያው አጋማሽ አኳያ ወረድ ያሉ ፉክክሮችን ያስመለከተን ብቻም ሳይሆን ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ጭምር ነበር። ማሜሎዲ ሰንዳውንሶች በመጠኑ ለኋላ ክፍላቸው ሽፋንን በመስጠት በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ባደረጉበት ወቅት በአማካዩዋ ዱሬቲ እና ራባሌ አከታትለው ያደረጓቸው እ በግብ ዘቧ ታሪኳ በርገና እና በቋሚ ብረቱ ከጎልነት ከተመከቱት ሙከራዎቻቸው ውጪ ዕድሎች በበቂ ሁኔታ ተፈጥረው ያልተስተዋለበት ነበር።

መከላከላቸው ላይ ዕርምት ቢወስዱም ማጥቃት ላይ ደካሞች የነበሩት የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ተጫዋቾ ሦስተኛው ሜዳ ላይ ሲገኙ በቁጥር አንሰው መታየታቸው ወደ ጨዋታ ቅኝት እንዳይገቡ ዕክል ሆኖባቸው አስተውለናል ፣ ሆኖም በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የ4ለ0 አሸናፊ ሆኖ ጨዋታውን ቋጭቷል።