👉 “ለውጦች ይመጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ…
👉 “ጋቶች ጥሩ ነገር ይሰራል ጠንካራ ተጫዋች ነው..
👉” ያሬድ ብርሀኑን አይተነዋል ስንከታተለው ነበር..
ከታንዛኒያ እና ዴሞክቲክ ኮንጎ ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ቡድናቸውን በማዘጋጀት ላይ ያሉት ዋና አሰልጣኙ መሳይ ተፈሪ በዛሬው ዕለት ለሚዲያ አካላት የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በከፊል ማቅረባችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ ስለተጫዋቾች ምርጫ የሰጡት ሀሳብ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ስለ ተጫዋቾች ምርጫ ባነሷቸው ነጥቦች ላይ “ከዚህ በፊት የሚጠሩ አሁን ያልመጡ ተጫዋቾች አሉ፤ ጋቶች ጥሩ ነገር ይሰራል ጠንካራ ተጫዋች ነው። በተለያዩ መንገዶች ከባላጋራም ካየኋቸው ነገሮች አንፃር መሻሻል አለባቸው ብለን ያደረግናቸው ነገሮች አሉ” ካሉ በኋላ ምርጫው ከጨዋታ እቅድ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ጠቅሰዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም በግብ ጠባቂዎች ምርጫ ላይ ተከታዩን ብለዋል ” ለታዳጊዎች ዕድል ከመስጠት አንፃር ሁለት ግብ ጠባቂዎች ተጠቅመን ሦስተኛው ተስፋ ያለው ተጫዋች አብዩ ካሳዬን ጠርተናል። እንዲሁም ያሬድን በቅርበት በደምብ ተከታትዬዋለሁ” ብለዋል።
“ቀድሞ የነበሩ የመከላከል ባህርያት አሉ በነበረው ላይም የጨመርኳቸው ነገሮች ይኖራሉ። የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ እና የቻን ማጣርያ ታሳቢ በማድረግ ነው ተጫዋቾቹን የመረጥናቸው። አሁን ላይ ውጤት ጋር በተያያዘ ከእናንተ የተሰወረ ነገር የለም አጥጋቢ አይደለም፤ ይህም ለማስተካከል እኔም ከእኔ ጋር በተለያየ ደረጃ ያሉ አካላት ጥረት እናደርጋለን። ለውጦች ይመጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ”።
አሰልጣኙ በመጨረሻም የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ እየመራ ስላለው ያሬድ ብርሀኑ ተከታዩን ሀሳብ ሰንዝረዋል” ያሬድን አይተነዋል ስንከታተለው ነበር፤ ይሄን ብቃት የሚቀጥል ከሆነ በቀጣይ የማይካተትበት ምንም ምክንያት አይኖርም፤ ጥሩ ነው እየሰራ ያለው” ብለዋል።