ወዋሎዎች የቀድሞ አሰልጣኛቸውን ዳግም በኋላፊነት ለመሾም ተቃርበዋል።
ቀደም ብለው ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር በስምምነት የተለያዩት እና አሰልጣኙን ለመተካት በእንቅስቃሴ ላይ የቆዩት ወልዋሎዎች የቀድሞ አሰልጣኛቸው ፀጋዬ ኪዳነማርያም አዲሱ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርገው ለመቅጠር ከጫፍ እንደደረሱ ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ታማኝ ምንጮች አረጋግጣለች።
ቡድኑ በሊጉ ደካማ አጀማመር ማድረጉን ተከትሎ ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር መለያየቱ የሚታወሰው ቡድኑ በሊጉ የመጨረሻው ጨዋታም በምክትሎቹ አታኽልቲ በርኸ እና ሀፍቶም ኪሮስ እየተመራ ወደ ሜዳ መግባቱ ይታወሳል። ላለፉት ቀናት ክለቡን የሚመራ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ሲንቀሳቀስ የቆየው የክለቡ የበላይ አመራር ሁለት አሰልጣኞችን ሲያነጋግር ከቆየ በኋላ በመጨረሻው ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ለመቅጠር ከጫፍ ደርሷል።
በ2010 የካቲት ወር ላይ ወልዋሎን በመረከብ በወቅቱ ቡድኑ በሊጉ እንዲቆይ ትልቅ ድርሻ ከተወጣ በኋላ በ2011 ጥር 21 በገዛ ፈቃድ ከኃላፊነት የተነሳው አሰልጣኝ ፀጋዬ ከዓመታት በኋላ ዳግም ወልዋሎን በሊጉ የማትረፍ ሀላፊነት ለመረከብ ተቃርቧል
በእርሻ ሠብል ያሳለፋቸውን አይረሴ አስራ ሦስት ዓመታትን ጨምሮ ለአስራ ስድስት ዓመታት በተጫዋችነት ካሳለፈ በኋላ በ1990 ‘ታክሲ’ በተባለ ቡድን የአሰልጣኝነት ህይወቱን የጀመረው ፀጋዬ ጊዳነማርያም ለሦስት ዓመታት በታክሲ ቡድን ከሰራ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚገኙ ክለቦች የመሥራት ጉዞውን በ1993 የአብሮ አደጉ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ምክትል በመሆን በትራንስ ኢትዮጵያ በመጀመር ከ1997 ጀምሮ በዋና አሰልጣኝነት በትራንስ ኢትዮጵያ ፣ ሐረር ቢራ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አርባምንጭ ከተማ፣ ወልዋሎ፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ጅማ አባጅፋር እና ወላይታ ድቻ አሰልጥኗል።
አሁን ደግሞ ከስድስት የሊግ ጨዋታዎች ነጥብ መሰብሰብ ያልቻለውን ወልዋሎን ወደ መልካም መንገድ የመመለስ ፈተና ይጠብቃቸዋል።