የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ893 ቀናት በኋላ በፉክክር ጨዋታ ድል አድርጓል።
በ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የምድቡ የመጨረሻ መርሃግብር የነበረው የምሽቱ መርሃግብር እጅግ ቀዝቃዛ አጀማመር የነበረው ሲሆን በመጀመሪያ አጋማሽ በ19ኛው ደቂቃ የዲ/ሪ ኮንጎው የግራ መስመር ተከላካይ ጆሪስ ካዬምባ ዲቱ ከሳጥን ጠርዝ በቀጥታ አክርሮ የሞከራት እና የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበረች።
አጋማሹም በተሻለ መንገድ ማጠናቀቅ የቻሉት ዋልያዎቹ በ36ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ ከቡድን አጋሮቹ የደረሰውን ግሩም ኳስ የዲ/ሪ ኮንጎውን የግብ ዘብ ሊዩኔል ምፓሴ ንዛዉን በማለፍ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።
ዋልያዎቹ ቀዳሚ በሆኑ በደቂቃዎች ልዩነት ብርሃኑ በቀለ ያገኘውን ግሩም አጋጣሚ ከግቡ አናት በላይ ሰደዳት እንጂ ለኢትዮጵያ ሁለተኛ ግብ መሆን የምትችል አጋጣሚ ነበረች።
የተዳከመውን ማጥቃታቸውን ለማሻሻል ሦስት አውንታዊ ለውጦችን በማድረግ አጋማሹን የጀመሩት ዲ/ሪ ኮንጎዎች ከመስመሮች ወደ ሳጥን በሚጣሉ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው በተፈለገው ልክ ፍሬያማ አልነበረም በአንፃሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተወሰኑ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎች ቢፈጥሩም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቸግረው የተስተዋለበት ነበር።
በድራማዊ ክስተቶች ታጅቦ ፍፃሜውን ባገኘው ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩት ሰባት ደቂቃዎች ዲ/ሪ ኮንጎዎች በዘጠና ሁለተኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ከተሻማ ኳስ ዲይላን ቡዱካ ሀገሩን አቻ ቢያደርግም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው መሀመድኑር ናስር በዘጠና ስድስተኛው ደቂቃ በግሩም አጨራረስ ዋልያዎቹን ባለድል አድርጓል።
የዛሬው ድልም ዋልያው ከአስራ ስምንት ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ዲ/ሪ ኮንጎን የረታበት ሆኖ ሲመዘገብ የዛሬው ድልም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሰኔ 2 2014 ግብፅን ሁለት ለባዶ ከረታበት ጨዋታ በኋላ በፉክክር ጨዋታ የተመዘገበ የመጀመሪያው ድል ሆኗል።