አሸናፊነትን የተላበሰ ብሔራዊ ቡድን እንዴት እንገንባ ?

በማቲያስ ኃይለማርያም እና ዳዊት ፀሐዬ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትላንት ምሽት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ጉዞውን አጠናቋል ፤ ቡድኑ ለ893 ቀናት የዘለቀውን የፉክክር ጨዋታ ድል ረሃብ ማስታገስ ቢችልም በምድቡ የመጨረሻ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል። የዝግጅት ክፍላችንም “ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በውጤት ማጣት ጉዞ መቀጠል ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?” በሚል ከቀናቶች በፊት ለተከታታዮቻችን ካዘጋጀነው መጠይቅ ተነስተን ተከታዩን ጽሁፍ አዘጋጅተናል።

እንደ ሀገር እጅግ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚፈስበት እግር ኳሳችን ከሚንቀሳቀሰው ገንዘብ በዘለለ ሌላ ትኩረትን የሚስብ አዎንታዊ ርዕሰ ዜና መፍጠር ከተሳነው ሰንብቷል ፤ ይባስ ብሎ የእግር ኳሳችን አይነተኛ ነፀብራቅ የሆነው ብሔራዊ ቡድናችን በፉክክር ጨዋታዎች ለመጨረሻ ጊዜ  ሰኔ 2፡ 2014 ግብፅን ሁለት ለባዶ ከረታ በኋላ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ 893 ቀናት ፈጅተውበታል።

ታድያ ብሔራዊ ቡድኑ እስከ ትናንትናው ጨዋታ ድረስ ላለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በፉክክር ጨዋታ 17 ጨዋታዎችን ቢያደርግም ማሸነፍ የቻለው የትናንትናው ጨዋታ ብቻ ነው። በእነዚህ አስራ ሰባት ጨዋታዎች ቡድኑ ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር በተቃራኒ ሃያ ስድስት ግቦች ዘንበውበታል።

በቅርቡ ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው እና በርካታ የእግር ኳስ ቤተሰቡ በተሳተፈበት የህዝብ መጠይቅ ከወቅታዊ የብሔራዊ ቡድኑ የውጤት አልባ ጉዞ በስተጀርባ አለ ስለሚሉት ምክንያት ባቀረብነው የህዝብ መጠይቅ 68% የሚሆኑት ምላሽ ሰጪዎች አሁናዊው የብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ማጣት የአጠቃላይ የሀገራችን እግር ኳስ ነፀብራቅ ስለመሆኑ ሀሳባቸውን ሲሰጡ ከምላሽ ሰጪዎቹ 28% የሚሆኑት ደግሞ ለቡድኑ ውጤት ማጣት ምክንያት ነው ብለው ያነሱት ጉዳይ የተጫዋቾች ብቃት ማነስን ሲሆን 18% ደግሞ በሜዳችን ያለመጫወታችን ለውጤት ማጣቱ እንደ ምክንያትነት ይቀርባል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የተቀሩት 6% የሚሆኑ ድምፅ ሰጪዎች ደግሞ ከውጤት መጥፋቱ በስተጀርባ ሌላ ምክንያት ስለመኖሩ ጠቁመዋል።

እርግጥ እግር ኳሳችን ፈርጀ ብዙ በሆነ የሜዳ እና የሜዳ ውጭ ጉዳዮች የታሰረ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው። የተሰበሰበው የህዝብ መጠይቅም እነዚህ ስር የሰደዱ የእግር ኳሳችን ችግሮች ተፅዕኗቸው በሁለንተናዊ የእግር ኳሳችን መልክ ላይ ስለማረፉ አይነተኛ ማስረጃ ነው።

የአሉታዊ ተፅዕኖ ደረጃቸው የሚለያይ ቢሆንም ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች የብሔራዊ ቡድኑ ተግዳሮቶች መሆናቸው ነጋሪ አያስፈልገውም። ሆኖም አጠቃላይ የሀገራችን እግር ኳስ ሁኔታ ለውጤት መጥፋቱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑ እሙን ነው። ችግሩ ከክለቦች ውጤት ተኮር፣ ራዕይ አልባ ጉዞ እና ደካማ አደረጃጀት እንዲሁም በአጠቃላይ በሀገሪቱ በተለያዩ ደረጃዎች የሚታየው የእግር ኳስ አስተዳደር መዋቅራዊ የተቋማት ችግር የመነጨ ነው። አንድ ሀገርን የሚወክል ብሔራዊ ቡድን የክለቦች ነፀብራቅ ነው። በክለቦች አደረጃጀት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግም እግር ኳሱን የሚያድነው ቀዳሚ ተግባር ነው። ሆኖም የክለቦቹን አሁናዊ ሁኔታ ሂደቱ የተወሳሰበ ያደርገዋል፤ የክለቦቹ አካሄድ ከታመመ ሰንበትበት ቢልም በተለይም ቅጥ ያጣው የገንዘብ አወጣጥ መንገዳቸው ከመንገዳገድ አልፎ ጠልፎ እንዳይጥላቸው ያሰጋል።

በመጠይቃችን ምላሽ ከሰጡ 28% የሚሆኑት ለቡድኑ ውጤት ማጣት ምክንያት ነው ብለው እንዳነሱት የተጫዋቾች ብቃት ማነስ ሌላው የብሔራዊ ቡድኑ ተግዳሮት ነው።

እዚህ ላይ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት መንበር በቆዩባቸው ጊዜያት በጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ካነሷቸው አንኳር ሀሳቦች መካከል በየሳምንቱ የተለያየ የብቃት ደረጃ ላይ ስለሚገኙት ተጫዋቾቻችን የገለፁት እንደ ማጣቀሻነት ማንሳት ይቻላል።
እንደ አሰልጣኙ አገላለፅ ተጫዋቾቻችን “በትንሽ ጭብጨባ” ከመንገድ ይስታሉ ሲሉም ተደምጠዋል። የተጫዋቾቻችን የብቃት እንዲሁም የወጥነት ችግር  ለማጠናከር የሶከር ኢትዮጵያን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጨዋታ ሳምንቱን ምርጥ ቡድን መመልከት አይነተኛ ምስልን ይፈጥራል። በቀናት ልዩነት በሚደረገው በዚህ ምርጫ በተከታታይ ሳምንታት በወጥነት የሚመረጡ ተጫዋቾችን ማግኘት እምብዛም የተለመደ አይደለም።

ታድያ ይህ ጉዳይ የእግር ኳሳችን ሀቅ በሆነበት የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች በእዚህ የተጫዋቾች ብቃት የወጥነት ችግር እና መውጣት መውረድ ውስጥ ሆነው ተጫዋቾችን እንዴት ባለ ሁኔታ ይመርጣሉ የሚለው ጉዳይ ሌላው መፍትሔ የሚሻ ነገር ነው።

ሌላኛው ከፍተኛ ድምፅ ያገኘው ምክንያት በሜዳችን ያለመጫወታችን ጉዳይ ነው፤ ይህ ሀሳብም 18% በሚሆኑ ድምፅ ሰጪዎች ዘንድ ለውጤት መጥፋቱ በምክንያትነት ይቀርባል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

እግር ኳሳችን ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚንቀሳቀስበት ቢሆንም ይህ የገንዘብ ፍሰት በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ ዛሬ ላይ ያተኮሩ ወይም ተቋም የማይገነቡ እና በእቅድ የማይመሩ ወጪዎች መሆናቸው የእግር ኳሳችን መሰረተ ልማት ቀድሞ ከነበረበት ደረጃ ፈቀቅ እንዳይል ምክንያት ሲሆን እየተመለከትን እንገኛለን። እግርኳሳችን በቢሊዮኖች የሚገመት በጀት የሚንቀሳቀስበት ቢሆንም በዘርፉ ያለው ስር የሰደደ ሙስና እና የገንዘብ አጠቃቀም ችግር በመሰረተ ልማት ላይ በቂ ያልሆነ ኢንቨስትመንት እንዲደረግ ምክንያት ሆኗል። በዋነኝነት በልማት እና የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ ግንባታ ላይ መዋል የነበረበት ገንዘብ በጊዝያዊ እና ራዕይ የሌለው የበጀት አጠቃቀም ድክመት ምክንያት ብሄራዊ ቡድኑ ለስደት ከመዳረጉ ባለፈ የፌደሬሽኑን ካዝና አራቁቶታል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ኢሳያስ ጅራ በቅርቡ በአንድ የሬዲዮ መሰናዶ ላይ ለአብነት ሲገልፁ እንደተደመጡት ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ ታንዜንያ ዳሬ ሰላም ላይ ላደረገው ጨዋታ ለሜዳ ኪራይ 20,000 ዶላር እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ ላይ ላደረጉት ጨዋታም እንዲሁ 90,000 ራንድ ወጪ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
ታድያ አሁንም በስደተኝነቱ የቀጠለው ብሔራዊ ቡድናችን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ሲጫወት ያገኝ የነበረውን ተጠቃሚነት የማጣቱ ጉዳይ ምን አልባት በቁጥራዊ መለኪያዎች መለካት ባይቻልም ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ የብሔራዊ ቡድናችንን የቅርብ ዓመታት ውጤቶች መመልከት በቂ ነው።

14% የሚሆኑ ድምፅ ሰጪዎች ደግሞ ለውጤት መጥፋቱ አሰልጣኞችን ተጠያቂ ያደረጉ ናቸው።

በአንድ ሀገር የእግር ኳስ እድገት የአሰልጣኞች ሚና ትልቅ ነው። አንጋፋው ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ ሪኑስ ሚሽየልስ በ1970ዎቹ የኔዘርላንድን እግር ኳስ ገፅታ የቀየሩበት አብዮታዊ ለውጥ እንዲሁም ስኬታማው አሰልጣኝ አሪጎ ሳኪ የጣሊያንን እግር ኳስ ባህል፣ የጨዋታ መንገድ እና የሥልጠና ዘዴዎች የለወጡበት መንገድ በጥልቀት ላስተዋለ የአሰልጣኞች ሚና ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ለመረዳት አያቅተውም። ይህንን በመንተራስ በጥቅሉ ስናየው በሀገራችን እግር ኳስ ውድቀት የአሰልጣኞች ድርሻም ቀላል እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል። አሰልጣኞች የደካማው የክለባች አደረጃጀት ሰለባ መሆናቸው የማይታበል ሀቅ ቢሆንም ዘመኑን የዋጀ የስልጠና እና የአጨዋወት መንገድ በማበጀት ረገድ ያላቸው ውስንነት በእግር ኳሱ እድገት አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል።

ይህ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ችግር በብሔራዊ ቡድኑ ውድቀትም የራሱ ድርሻ አለው። ከዚህ በተጨማሪ ብሔራዊ ቡድኑ በቅርብ ዓመታት በአንፃራዊነት የተሻለ ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ ከሚሰጡ አሰልጣኞች ወደ ለቀጥተኛ አጨዋወት የቀረበ የጨዋታ ዕቅድ ያላቸው አሰልጣኞች መሸጋገሩም ወጥነት ያለው እና የተቀናጀ አጨዋወት እንዳይኖረው እንዲሁም የውህደት ደረጃው እንዲዋዥቅ አድርጎታል።

እግር ኳሳችን በፈርጀ ብዙ ችግሮች የተተበተበ እንደመሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ሰፊ ጥናት እና ምርምር የሚጠይቅ የዓመታት ሥራ ቢሆንም የአብዛኛዎቹ ችግሮቹን መነሻ የሆነው እና የእግር ኳሱ ባለቤት የሆኑትን ክለቦች አደረጃጀት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ ግን ቅድምያ ሊሰጠው የሚገባ ወሳኝ ተግባር ነው። ክለቦቹ በጥቂት ግለ-ሰብ ላይ ጥገኛ የሆነ እና ተቋማዊ ባልሆነ አደረጃጀት መመራታቸውም በሜዳም ይሁን ከሜዳ ውጭ ያለውን የእግር ኳሱ ሁኔታ ክፉኛ ደቁሶታል። የአንድ ሀገር ብሄራዊ ቡድን ውጤታማነት ከክለቦች እድገት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ትስስር አለው። የክለቦቹ ኋላ ቀር አደረጃጀት ላይ ለውጥ ማድረግም የወጣት ተጫዋቾች እድገት ማሳለጥ፣ የምልመላ ስርዓት ለማስተካከል፣ ለአሰልጣኞች ምቹ የስራ ከባቢ መፍጠር እንዲሁም በክለቦቹ አሰራር የተጠያቂነት እና ፍትሐዊ የስራ ክፍፍል እንዲኖር ያስችላል።