የዋልያዎቹ አለቃ መሳይ ተፈሪ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዙርያ ምን አሉ?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የምድቡን የመጨረሻ መርሃግብሮች በታንዛኒያ 2-0 ተሸንፎ ዲ/ሪ ኮንጎ ደግሦ 2-1 ረቶ መመለሱን ተከትሎ በጨዋታዎቹ ዙርያ የዋልያዎቹ ጊዜያዊ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለመገናኛ ብዙኃን በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዲ/ሪ ኮንጎን ለማሸነፍ የረዳቸውን የምክንያት ሲያብራሩ “የተጋጣሚያችንን የጨዋታ መንገድ ምን እንደሆነ በደንብ ተረድተን መምጣታችን ለድሉ አስተዋፆኦ ነበረው። ተጫዋቾቻችንም ታክቲካሊም፣ እንችላለን የሚል ጠንካራ በራስ መተማመን የነበራቸው በመሆኑ ከታዛኒያው ሽንፈት ማግስት ወደ ድል ተመልሰናል።” ካሉ በኋላ ዲሞክራቲክ ኮንጎን ማሸነፋቸው ብዙ ትርጉም እንዳለው ሲናገሩ“ ለእኔም ሆነ ለተጫዋቾቹ አጠቃላይ ለቡድኑ አባላት ድሉ ብዙ ትርጉም አለው። ከተከታታይ ሽንፈት አይደለም ሁለት ጨዋታ በተከታታይ መሸነፍ ከባድ እስራት ውስጥ ነው የምትገባው። ከዚህ አንፃር ድሉ ከዚህ ሽንፈት ለመውጣት፣ በቀጣይ በቻን አፍሪካ ዋንጫ ከሱዳን ጋር ለምናደርገው ጨዋታ በተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ መነሳሳት ይፈጥራል። ለማሸነፍ ምንም የሚከለክለን ነገር የለም ስራ ነው የሚፈልገው ጠንክሮ መስራት አለብን” ብለዋል።

አሰልጣኙ አክለውም “በአጋጣሚ የመጣ ውጤት ነው ለሚለው ውጤቱ በአጋጣሚ ፣በስሜት፣ በእውቀት የመጣ ውጤት መሆኑ በቀጣይ ጨዋታ እናየዋለን። ለየትኛውም ነገር ጊዜ አስፈላጊ ነው። አዲስ አሰልጣኝ ሲመጣ አንድ ነገር ሲሰራ ከተጫዋቾቹ  ለመግባባትም ጊዜ ያስፈልጋል”ብለዋል።
 
በመጨረሻም አሰልጣኙ በቀጣይ ከሃያ ቀናት በኋላ ከሱዳን አቻቸው ጋር ስላለባቸው የቻን አፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ሲናገሩ“ የምንዘጋጀውም ሆነ የምንሰራውም ቻን ለማለፍ አስበን ነው።” በማለት ተናግረዋል።