ለአህጉራዊ ውድድር አስራ ሦስት ያህል ቀናትን ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በነገው ዕለት በሚደረጉ ሁለት መርሐግብሮች የሚመለስ ሲሆን እኛም በጥንቅራችን የጨዋታዎቹን መረጃዎች ይዘንላችሁ ቀርበናል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ
ሊጉ ከተቋረጠ በኋላ ዳግም ሲመለስ በድል እና በሽንፈት አገባደው የነበሩ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ ቀዳሚ የትኩረት ነጥባችን ይሆናል።
ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም በተመለሱበት የመጀመሪያ ዓመታቸው ላይ የሚገኙት አርባምንጭ ከተማዎች አራፊ የነበሩበት ሳይቆጠር እስከ አሁን ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለት ድል ፣ ሦስት ሽንፈት እና የአንድ የአቻ ውጤቶችን በማስመዝገብ በደረጃ ሰንጠረዡ አስራ አምስተኛ ላይ መቀመጥ የቻሉ ሲሆን በነገውም ዕለት በስምንተኛ ሳምንት መርሐግብራቸውን ከሀገራት የማጣሪያ ጨዋታዎች መልስ ወልዋሎን ይገጥማሉ። በተከታታይ አሸናፊ ከሆኑ በኋላ በመጨረሻው የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ 1ለ0 መረታት የቻሉት አዞዎቹ ለቀናቶች በነበራቸው የዕረፍት ጊዜያቸው በመልሶ ማጥቃት የሚጫወቱበትን አቀራረብ ዳግም እንደሚያስመለክቱን የሚጠበቅ ቢሆንም በአዲስ አሰልጣኝ ስር የመጀመሪያ ሦስት ነጥብን ለማሳካት የሚገቡት ወልዋሎን እንደመግጠማቸው ሊገጥማቸው የሚችለው ፈተና ቀላል አይሆንም ፤ ቢሆንም የተጋጣሚያቸውን የመስመር መከላከል ድክመትን መጠቀም ከቻሉ ግን አንዳች ነገርን መፍጠራቸው አይቀርም።
በከፍተኛው የሀገራችን የሊግ ዕርከን ላይ እየተካፈሉ ካሉ ቡድኖች ውስጥ በብዙ መመዘኛ ደካማ መሆናቸውን ባደረጓቸው ጨዋታዎች ላይ ሁሉ ያስመሰከሩት ወልዋሎ ዔዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች ከናፈቃቸው ነጥብ ጋር ለመገናኘት በአዲሱ አሰልጣኛቸው ፀጋዬ ኪዳነማርያም መሪነት ወደ ሜዳ የሚገቡ ይሆናል። በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በአምስት በጊዜያዊ አሰልጣኞቹ አታክልቲ በርኸ እና ሀፍቶም ኪሮስ ደግሞ አንድ ጨዋታ በድምሩ በስድስት ጨዋታዎች ሽንፈት በመቅመስ በ8 የግብ ዕዳ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች በአዲሱ አሰልጣኝ በአዲስ ዕሳቤ እና በአዲስ የጨዋታ አቀራረብ ይገባሉ ተብሎ ይታመናል። በማጥቃቱም ይሁን በመከላከሉ ረገድ ብዙ መሻሻሎች የሚያስፈልጋቸው ወልዋሎ ዓዲግራቶች አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ከዚህ ቀደም በመሯቸው ቡድኖች ውስጥ የነበራቸውን ከመከላከል በፍጥነት በረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት የሚመርጡትን የጨዋታ መንገድ ነገም እንደሚያስመለክቱን መገመት ቢያሻም ከተጋጣሚያቸው የመከላከል ጥንካሬ አንፃር ቀላል የሚባል ፈተና ሊያስተናግዱ እንደማይችሉ ግን መገመት ያሻል።
በአዞዎቹ በኩል አበበ ጥላሁን የነገው ጨዋታ ያመልጠዋል ፣ ይሁን እንዳሻው ከጉዳት አገግሞ የሚመለስ ሲሆን የቻርለስ ሪባኑ የመሰለፍ ጉዳይ ግን አጠራጣሪ ሆኗል። በአዲሱ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የሚመሩት ወልዋሎዎች በበኩላቸው ናትናኤል ዘለቀ ፣ ኤፍሬም ጥላሁን ፣ ሳምሶን ኃይለማርያም ፣ አላዛር ሽመልስ እና ስምዖን ማሩን በጉዳት እንዲሁም በረከት አማረን በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ወልዋሎዎች አንድ ድል ሲያስመዘግቡ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ወልዋሎ አራት በአንፃሩ አርባምንጭ አንድ ጎልን በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ
ሁለቱን ድል ናፋቂ ቡድኖችን ነገ ምሽት የሚያፋልመው ጨዋታ ቀጣዩ የዳሰሳችን አካል ነው።
በአራተኛውም ሆነ በአምስተኛው ሳምንት ጨዋታ በአዳማ እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ ሽንፈት አስተናግደው በመጨረሻ ጨዋታቸው አራፊ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በሁለት ድል ፣ በሦስት ሽንፈቶች እና በአንድ የአቻ ውጤት ቀስ በቀስ ተንሸራተው በደረጃ ሰንጠረዡ 17ኛ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በከተማው ከሚጫወተው ድሬዳዋ ከተማ ጋር ነገ አመሻሹን ይፋለማሉ። ሲዳማ ቡናን በመጀመሪያ ሳምንት በረቱበት ወቅት በመከላከሉ ላይ ጠጣር የሆነ አቀራረብን አሳይተውን የነበሩት ሐይቆቹ በቀጣዮቹ ጨዋታዎቻቸው ላይ ግን ተጋላጭ እየሆኑ ከመምጣት ባለፈ በቀላሉ ግቦችን ሲያስተናግዱ ተስተውሏል ፣ ዓሊ ሱለይማንን በመጠቀም ቀጥተኛ አልያም ፈጣን ሽግግር በመጠቀም ለማጥቃት የሚዳዳው ቡድኑ ከዚህ የጨዋታ መንገድ ብዙም ያልራቀን አቀራረብ ነገ ያሳየናል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም በተቃራኒው መከላከላቸው ላይ በተደጋጋሚ የሚያሳዩትን የመናበብ ክፍተት መድፈን ካልቻሉ ግን ፈጣን በሆኑ የመስመር አጥቂዎቻቸው በሚታገዙት ድሬዳዋ ከተማ መቀጣታቸው የሚቀር አይመስልም።
በመጀመሪያ ተከታታይ ሁለት መርሐግብሮች ላይ ሁለት ድሎችን ወደ ቋታቸው ከከተቱ በኋላ ላለፉት አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ከድል ጋር የተራራቁት ድሬዳዋ ከተማዎች ነገ የዓመቱ ሦስተኛ ድላቸውን ማስመዝገብን እያለሙ ከሌላኛው የውጤት ረሃብ ውስጥ ከሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ጋር በብርቱ ለመፋለም ይገባሉ። ከስድስት ጨዋታዎቻቸው በሁለት ድል ፣ በሁለት ሽንፈቶች እና በሁለት አቻዎች ስምንተኛ ደረጃ ላይ ረግተው የተቀመጡት ብርቱካናማዎቹ በማጥቃት አቀራረባቸው የተሻሉ ቢሆኑም መጠነኛ ዝንጉነት የሚታይባቸው የቅብብል ስህተቶቻቸው እና በመስመር መከላከሉ ላይ ያለባቸውን ድክመቶች ማረም ከቻሉ ግን በድጋሚ ወደ ውጤት መንገድ መመለሳቸው አይቀርም ፤ ይሁን እንጂ የሚገጥሙት ሌላውን ውጤት ናፋቂውን ሀዋሳ ከተማን እንደመሆኑ ሜዳ ላይ የሚጠብቃቸው ፍክክር ግን በእጅጉ ጠጣር እንደሚሆን ይጠበቃል።
ሀዋሳዎች ቅጣት ላይ የሚገኘውን እንየው ካሳሁንን ሲያጡ ድሬዳዋ ከተማዎች በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ከሆነው ያሬድ ታደሰ ውጭ ከቅጣትም ሆነ ጉዳት ነፃ የሆነው ስብስባቸው ይዘው ለነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።
ሁለቱ ክለቦች ነገ በሊጉ ለ25ኛ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች 9 ፣ ድሬዳዋ ከተማዎች 6 ድል አስመዝግበው በ9 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሐይቆቹ 28 ግቦችን ሲያስቆጥሩ ብርቱካናማዎቹ ደግሞ 21 ግቦችን ከመረብ አገናኝተዋል።