አርባምንጭ ከተማ ወልዋሎን በመርታት ደረጃውን ያሻሻለበት ድል አስመዝግቧል።
አርባምንጭ ከተማዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ አሰላለፍ አበበ ጥላሁን፣ ቻርለስ ሪባኑ፣ ይሁን እንደሻው እና ቡታቃ ሸመናን በአሸናፊ ፊዳ፣ መሪሁን መስቀለ፣ አንዱዓለም አስናቀ እና እንዳልካቸው መስፍን ተክተው ሲገቡ ወልዋሎዎችም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት ካስተናገደ ቋሚ አሰላለፍ ሱልጣን በርኸ በጋዲሳ መብራቴ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ በወሰዱበት አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር እንዲሁም በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። ስቴፋን ባዱ ከመዓዘን ምት የተሻገረችውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ባደረጋት ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት አዞዎቹ በሙከራ ረገድ የበላይነት ወስደዋል።
በሀያ ሁለተኛው ደቂቃም ጥረታቸው ሰምሮ ጨዋታውን መምራት ችለዋል፤ አሸናፊ ተገኝ ከግራ መስመር የተቀበላትን ኳስ ለበፍቅር ግዛው አቀብሎት የመስመር አጥቂው ከሳጥኑ ጠርዝ አከባቢ በግሩም ሁኔታ ዞሮ ያስቆጠራት ግብም ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ነበረች።
ከግቧ መቆጠር በኋላም ሙከራዎች በማድረግ ረገድ የተሻሉ የነበሩት አርባምንጮች አሸናፊ ተገኝ ከሳጥኑ ውጭ አክርሮ በመምታት ባደረጋት ሙከራ እና አሕመድ ሁሴን የግብ ጠባቂውን መውጣት ተከትሎ ከፍ አድርጎ ለማስቆጠር በሞከራት ሙከራ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። በሂደት ውስን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተጠግተው የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲቸገሩ የታዩት ወልዋሎዎች ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ሙከራ ሳያደርጉ ከቆዩ በኋላ በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ለግብ የቀረበች ሙከራ አድርገዋል። ዮናስ ገረመው ከግራ መስመር አሻምቷት ቡልቻ ሹራ በግንባሩ ገጭቷት ፋሪስ አለዊ ግብ ከመሆን ያገዳት ኳስም ቢጫዎቹን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።
ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረገበት እና ወልዋሎዎች በኳስ ቁጥጥር ረገድ ብልጫ የወሱደበት ሁለተኛው አጋማሽ ግብ ያስተናገደው ጨዋታው በተጀመረ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ነበር። አሕመድ ሁሴን ስቴፋን ባዱ ከተከላካይ መስመር በረዥሙ ያሻገረለትን ኳስ በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም የአዞዎቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ያደረገች ነበረች።
ወልዋሎዎች በአጋማሹ በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻለ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል በነበራቸው የፈጠራ ችግር ወደ ግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በአጋማሹም ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ መኮንን በግብ ጠባቂው ስህተት ታግሎ ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ ካደረጋት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል የጠራ ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ አዞዎቹ በፈረሰኞቹ ከደረሰባቸው ሽንፈት በማገገም ድል አድርገው ነጥባቸው አስር ስያደርሱ ወልዋሎዎች አሁንም ነጥብ ማስመስገብ ያልቻሉበት ሳምንት ሆኖ አልፏል።