ሁለት ከድል የራቁ ቡድኖችን ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ መስዑድ መሐመድ በመጨረሻዎቹ ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ፍፁም ቅጣት ምት ግብ ብርቱካናማዎቹ ሀይቆቹን ረተዋል።
ሀዋሳ ከተማ በስድስተኛው ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ባደረጓቸው ለውጦች እንየው ካሳሁን ፤አቤነዘር ዩሀንስ እና እስራኤል አሸቱን አሳርፈው በምትካቸው ፊቃደስላሴ ደሳለኝ ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና ተባረክ ሔፋሞን ይዘው ሲገቡ ድሬዳዋ ከተማ በአንፃሩ በሰባተኛው ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና ከተረታው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ መስዑድ መሐመድን በሄኖክ ሀሰን ተክተው ቀርበዋል።
በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ ፋክክር በማድረግ በፈጣን ሽግግር ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ያደረጉበት ነበር። በዚህም ወደ ብርቱካናማዎቹ ግብ ክልል መድረስ የቻሉት ሀይቆቹ 7ኛው ደቂቃ ላይ በዓሊ ሱሌማን ላይ በተሰራ ጥፋት ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ቅጣት ምት አግኝተው ቀጥታ ወደ ግብ ቢመቱም የድሬዳዋ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውባቸዋል። ብርቱካናማዎችም በበኩላቸው ግብ አስቆጥረው መሪ ለመሆን ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት አድርገዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ በመጣው በአጋማሹ ቡድኖቹ ግብ ለማስቆጠር ወደ ፊት ከመሄድ ይልቅ ግብ ላለማስተናገድ በጥንቃቄ ተጫውተዋል።
አጋማሹ ወደ መጠናቀቂያው ሲቃረብ መነቃቃት ሲታይ በ37ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልሰላም የሱፍ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ የመታት ኳስ ለትንሽ ወደ ውጪ የወጣችበት አጋጣሚ የብርቱካናማዎቹ የመሪነት ጉጉት እውን ለማድረግ የቀረበ ሙከራ ነበር። በ41ኛው ደቂቃ ላይ በሀይቆቹ በኩል ቢኒያም በላይ በግራ መስመር በኩል ያሻገራትን ኳስ ዓሊ ሱሌይማን ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ ተብሎባቸዋል።
ጨዋታው ከእረፍት ሲመለስ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ድሬዳዋ ከተማዎች ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ አድርገዋል።
በሁለተኛ አጋማሽ ቡድኖቹ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ጨዋታው በሙከራዎች መታጀብ ግን አልቻለም። ብርቱካናማዎቹ በኳስ ቁጥጥር ረገድ ብልጫ ወስደው በቅብብል ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን የመሐል ሜዳ ላይ ቁጥጥር ለመውሰድ በሚመስል መልኩ የተጫዋቾች ቅያሪ አድርገው ጫና ፈጥረው ወደ ፊት ለመድረስ ሲጥሩ ተስተውለዋል።
ሀይቆቹ በአንፃሩ በመልሶ መጥቃት ወደ ብርቱካናማዎቹ ነሚያርጉትን ግስጋሴ በብርቱካናማዎች ተከላካዮች በቀላሉ ሲገቱ ተስተውሏል።
እምብዛም የግብ ሙከራ ባላስመለከተው በአጋማሹ ብርቱካናማዎቹ በኳስ ቁጥጥር በላይነት ወስደው ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሲቃረብ መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት ድሬዎች ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ወደ ግብ ቀይረው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከናፈቁት ድል ጋር ተገናኝተዋል።
89ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ መስመር በኩል መሐመድኑር ናስር ኳስ ይዞ ወደ ሀይቆቹ ግብ ክልል በሚገባበት ወቅት ፊቃደስላሴ ደሳለኝ በሰራው ግልፅ ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ለብርቱካናማዎቹ ተሰጥቶ ተቀይሮ የገባው መስዑድ መሐመድ ፍፁም ቅጣት ምቱን አስቆጥሮ ብርቱካናማዎቹን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አስገኝቷል።