ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ተከታታይ 3ኛ ድል አሳክቷል

በምሽቱ መርሐግብር ኢትዮጵያ መድኖች ከዕረፍት መልስ በተቆጠሩ ጎሎች አዳማ ከተማን 2ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

ሊጉ ከመቋረጡ በፊት አዳማ በመቻል ሽንፈት ካስተናገደው ስብስባቸው ሙሴ ኪሮስ ፣ ነቢል ኑሪ እና ቢኒያም ዐይተንን በማሳረፍ ሱራፌል ዐወል ፣ አድናን ረሻድ እና አሜ መሐመድን መተካት ሲችሉ መድኖች በመቐለ ላይ ድል ከተቀናጀው ቋሚያቸው ውስጥ ያሬድ ካሳዬን በአብዲሳ ጀማል ብቸኛ ያደረጉት ለውጣቸው ሆኗል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ግን የማጥቃት ደመ ነብሱ መቀዛቀዝ የነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ አምስቱን ቀዳሚ ደቂቃዎች በመስመር ፈጥነው ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ላይ የተገኙት አዳማዎች በአሜ መሐመድ ፈጣን ጥቃትን ሰንዝረዋል። ረጃጅም የሆኑ ኳሶችን ተጠቅመው ማጥቃትን በተመሳሳይ ምርጫቸው ያደረጉት ሁለቱም ቡድኖቹ መድኖች ከቅጣት ምት በዳዊት ተፈራ አማካኝነት ሁለተኛዋን ሙከራ አድርገዋል።

ከፉክክር አኳያ ወረድ ከማለቱ በተጨማሪ በሙከራዎች ብዙም መድመቅ የተሳነው ጨዋታው 24ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ትኩረት የሚስብ ክስተትን አሰመልክቶናል። የአዳማ እና የመድን የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የሆኑት ፍቅሩ አለማየሁ እና ዋንጫ ቱት ዕርስ በዕርስ መሐል ሜዳው ላይ በፈጠሩት ሰጣገባ የዕለቱ ዋና ዳኛ አለማየሁ ለገሠ ሁለቱንም ተጫዋቾች በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ያሰናበቷቸው ሲሆን የመድኑ ዋንጫ ቱት የዓመቱ ሁለተኛ ቀይ ካርዱ ሆኖ ተመዝግቦበታል።

ከቀይ ካርዱ በኋላ ባሉት ደቂቃዎች መጠነኛ መነቃቃቶች የተስተዋለበት ጨዋታው 26ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የአዳማ ከተማው ስንታየሁ መንግሥቱ ያመለጠችውን ያለቀላት ኳስን ከጀርባ ያገኘው አሜ ወደ ግብ ሲመታ የግብ ዘቡ አቡበከር ኑራ በጥሩ ብቃት ከግብነት አግዷታል። አጋማሹ ሊገባድ በተሰጠው ጭማሪ ላይ መድኖች በጥሩ የእግር ሥራ ሳጥን ደርሰው ከዳዊት ያገኛትን ኳስ አቡበከር ሳኒ የግቡ አፋፍ ላይ ሆኖ የመታትን ኳስ ወደ ውጪ ሰዷታል።

ከዕረፍት ሲመለስ መጠነኛ የአቀራረብ ለውጦች በነበሩት ጨዋታ ቀስ በቀስ ግን መድኖች የተሻለውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የያዙበት ነበር። በእንቅስቃሴ ፈጥነው ሳጥን የደረሱት አዳማ ከተማዎች 51ኛው ደቂቃ አድናን ከግራ ወደ ውስጥ ያቀበለውን ስንታየሁ በዝንጉነት ካመከናት ከሁለት ደቂቃ መልስ ግብ አስተናግደዋል። ጋቶች ፓኖም ከቀኝ ያስጀመራት ኳስን ረመዳን የሱፍ በጥሩ ቅብብል ከአቡበከር ሳኒ ጋር ተቀባብሎ በግሩም አጨራረስ ጎልን በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች አዳማ ከተማ ረጃጅም ኳስን መድኖች በይበልጥ በሽግግር ላይ ያተኮረውን አጨዋወት በመጠቀም ልዩነት ለመፍጠር በብርቱ የታገሉበት ነበር። መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ተቋጭቶ በተሰጠው ጭማሪ ላይ ተቀይሮ የገባው መሐመድ አበራ 90+1′ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ሁለተኛዋን ጎል ካስቆጠረ በኋላ የመድኑ የመሃል ተከላካይ ሚሊዮን ሰለሞን በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሲወገድ በመጨረሻም ጨዋታው በኢትዮጵያ መድን 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉም ለቡድኑ ተከታታይ 3ኛ ሆኖ ተመዝግቦለታል።