የጨዋታ ሪፖርት ፡ ወልድያ 1-0 ዳሽን ቢራ

በመሃመድ አህመድ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታ ወልድያ የመጀመርያ የሊግ ጨዋታውን አሸንፏል፡፡ ወልድያ መልካ ኮሌ ላይ ዳሽን ቢራን ባስተናገደበት ጨዋታ ከውጠት መጥፋት ጋር በተያያዘ በርካታ ደጋፊዎች ወደ ስታድየም ያልመጡ ሲሆን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያሳደጉት አሰልጣኝ ንጉሴ ኃይሉ ተሰናብተው በምትካቸው የቴክኒክ ዳይሬክተሩ ሚልዮን ታዬ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ቡድኑን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃ ወልድያዎች በአቅሌሌያስ ግርማ አማካኘነት ግብ ሊሆን የሚችል የግብ እድል የፈጠሩ ሲሆን በግብ ጠባቂው ደረጄ ጥረት ግብ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

ዳሽኖች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ቢሆኑም ወልድያዎች በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ በመድረስና የግብ እድል በመፍጠር በኩል ተሸለው ታይተዋል፡፡ በ24ኛው ደቂቃ ዳሽኖች ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ በሚል ሲሻርባቸው ከደቂቃዎች በኋላ አስራት መገርሳ ከረጅመ ርቀት ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዘውዱ መስፍን አምክኖበታል፡፡

ከአስራት ሙከራ በኋላ በመጀመርያው አጋማሽ ይህ ነው ሊባል የሚችል የግብ ሙከራ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ሳይደረግ የመጀመርያው አጋማሽ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ የወልድያው አምበል ተስፋ ሚካኤል በጉዳት በእድሪስ አሲድ ተቀይሮ ሲወጣ በ50ኛው ደቂቃ በወልድያ ተከላካዮች ስህተት የተገኘቸውን ኳስ መድህኔ ታደሰ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ የሆነ ግልፅ የግብ እድል ቢያገኝም ዘውዱ መስፍን በግሩም ሁኔታ ግብ ከመሆን አግዷታል፡፡

ወልድያ ታጁዲንን ዳሽን ደግሞ ዮናታን ከበደን ቀይረው በማስገባት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ሁለቱም ቡድኖች ግልፅ የግብ እድል መፍጠር ተስኗቸው ታይቷል፡፡

በ77ኛው ደቂቃ የዳሽኑ ፉልባክ ዳዊት ሞገስ በእድሪስ ሰኢድ ላይ በሰራው ጥፋት ከሜዳ በቀይ ካርድ ሲወጣ የተገኘውን ቅጣት ምት ተከላካዩ ፍሬው ብርሃኑ ወደ ግብ ቀይሮ ወልድያን መሪ አድርጓል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኋላ ወልድያ አጥቂው አብይ በየነን አስወጥቶ በዳሶ ሆራን በማስገባት ቀሪዎቹን 13 ደቂቃዎች በጥልቀት የተከላከሉ ሲሆን መሪነታቸውን አስጠብቀው ወጥተዋል፡፡

በጨዋታው የእለቱ አርቢትር ለወልድያ ተጫዋች 1 ቢጫ ሲያሳዩ በዳሽን ተጨዋቾች ላይ ሁለት የማስጠንቀቅያ እና 1 ቀይ ካርድ መዘዋል፡፡

ወልድያ ከ7 አመታት በኋላ በሁለት የአማራ ክለቦች መካከል የተደረገውን ጨዋታ በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣ የሚያደርገውን ትግል ቀጥሏል፡፡

ያጋሩ