ሪፖርት | መቻሎች በጭማሪ ደቂቃ በተገኘች ግብ በኤሌክትሪክ ከመሸነፍ ተርፈዋል

ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሊጉን መሪነት ሊረከብ የሚችልበትን ዕድል በጭማሪ ደቂቃ ባስተናገደው ግብ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።


ኤሌክትሪክ ከፋሲሉ የ3ለ2 አሸናፊ ስብስባቸው በፍቃዱ አስረሳኸኝን በሔኖክ ፍቃዱ እንዲሁም መቻሎች ከአዳማ ከተማ የ2ለ0 ድላቸው በተመሳሳይ ዓለምብርሀን ይግዛውን በአስቻለው ታመነ ብቸኛ ለውጦቻቸው በማድረግ ለጨዋታው ቀርበዋል።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከፍታ ላይ ያሉትን የመዲናይቱን ሁለት ቡድኖች ያገናኘው የምሽቱ መርሐግብር በብዙ ረገድ መቻሎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በቀላሉ ወደ ተጋጣሚያቸው ሦስተኛ የሜዳ ክፍል መድረስ የቻሉበት በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ወደ ኋላ አፈግፍገው በተወሰኑ አጋጣሚዎችን ግን በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም የሞከሩበትን ሂደት አስተውለናል።

ሜዳውን በይበልጥ በመለጠጥ በጥሩ የኳስ ቅብብሎች የሚጫወቱት መቻሎች ምንይሉ ወንድሙ ከሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት አክርሮ መቶ የግብ ዘቡ ኢድሪሱ አብዱላሂ ተፍቶ በድጋሚ ኳሷን ያገኘው አቤል ነጋሽ የሞከራት አጋጣሚ ቀዳሚዋ ሙከራቸው ነበረች ፤ ግለቱን ወደ ጠበቀ እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ የገባው ጨዋታ ጥሩ የማጥቃት ሽግግሮችን ያሳየን ቢሆንም ጥራት ያላቸውን የግብ አጋጣሚዎችን ግን እምብዛም አላስመለከተንም።

ጨዋታው 30ኛውን ደቂቃ ሲሻገር የኤሌክትሪኩ አማካይ ሀብታሙ ሸዋለም ባገጠመው ጉዳት በቢኒያም በቀለ ተተክቶ ወጥቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ መቻሎች መሪ ሊሆኑ የሚችሉበት መልካም ዕድል ፈጥረው ነበር። 

ግሩም ሐጎስ ከቀኝ መስመር የሰጠውን ኳስ አብዱልከሪም ሳጥን ውስጥ ለተገኘው አማኑኤል ሰጥቶ ተጫዋቹም ወደ ጎልነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ ተከላካዩ አብዱላዚዝ አማን ደርሶ ያስጣለው ትኩረት የነበራት ጠንካራ ሙከራ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲቀጥል ተመጣጣኝ ፉክክሮች የነበሩበት እና የማጥቃት ፍላጎቶች ከፍ ብለው የታየበት ቢሆንም ዕድሎችን በቀላሉ ለማግኘት የቡድኖቹ የመከላከል አደረጃጀት ግን ጠጣር ነበር።

ጥሩ እንቅስቃሴን ማስመልከቱን በቀጥለው ጨዋታ ኤሌክትሪኮች 57ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ሽግግር ያገኙትን ኳስ ሽመክት ጉግሳ ወደ ግራ ላዘነበለው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ አሾልኮለት በድንቅ አጨራረስ አጥቂው ጎል አድርጎ ቡድኑ መሪ አድርጓል።

ጎልን ካስተናገዱ በኋላ አከታትለው የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የበላይነቱን ይዘው የታዩት መቻሎች 72ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ፍሪምፓንግ መቶ ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ አብዱላሂ ያዋጣበት እና ከማዕዘን ያገኘውን ሽመልስ ሳይጠቀምባት የቀረው አጋጣሚ ቡድኑን ወደ አቻነት ሊያሸጋግሩ የተቃረቡ ዕድሎቻቸው ነበሩ።

ያሳዩ እንደነበረው የጎላ እንቅስቃሴ የኤሌክትሪክን ተከላካዮች ማስከፈት ከብዷቸው የነበሩት መቻሎች በመጨረሻም ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ 90+2 ላይ ሽመልስ በቀለ በሳጥን ውስጥ በተሰራ ጥፋት የተገኘን የፍፁም ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ ከመረብ አሳርፎ ጨዋታው በአንደ አቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።