8ኛ ሳምንት ነገ ፍፃሜውን ያገኛል፤ የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ መርሃግብሮችን አስመልክተን ያዘጋጀናቸው መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርቧል።
ወላይታ ድቻ ከ ፋሲል ከነማ
የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር ወደ ሊጉ መሪነት ከፍ ለማለት የሚያስችላቸውን ሦስት ነጥብ ፍለጋ ወደ ሜዳ የሚገቡት የጦና ንቦቹ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ካስተናገዱት ዐፄዎቹ ያገናኛል።
በሊጉ በወቅታዊ ብቃት ደረጃ ምርጥ ብቃት ላይ ካሉት ቡድኖች ተርታ የሚመደቡት ወላይታ ድቻዎች ከተከታታይ ሦስት ድሎች መልስ ካስመዘገቡት የአቻ ውጤት ተላቀው ዳግም ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በ3ኛው እና 4ኛው ሳምንት ላይ ተከታታይ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ ባከናወኗቸው አራት ጨዋታዎች ላይ ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች አስሩን ያሳኩት የጦና ንቦች በድምሩ አስራ ሦስት ነጥቦች በመሰብሰብ በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በመጀመርያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች በማስተናገድ አስከፊ አጀማመር ያደረገው ቡድኑ በሂደት ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ገንብቷል ፤ ይህንን ተከትሎም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። የነገው ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ በሊጉ አናት መቀመጥ የሚችሉበት እንደመሆኑም ወሳኝነቱ ትልቅ ነው።
ሊጉን በጀመረበት የድል መንገድ መቀጠል ያልቻለው ፋሲል ከነማ ድል ማድረግ ከተሳነው ስድስት ጨዋታዎች አልፈዋል።
ቡድኑ ነጥብ በጣለባቸው ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ማስቆጠር ቢችልም በመጨረሻው መርሃግብር ግን የተሻለ የፊት መስመር ጥንካሬ ነበረው።
ከዚህ በተጨማሪም በሁነኛ ግብ አስቆጣሪ እጦት ሲቸገር የተስተዋለው ቡድኑ ጌታነህ ከበደ ወደ ግብ አስቆጣሪነት መመለሱ ጥሩ ዜና ነው። የተከላካይ መስመሩ ቡድኑ አሁን ካለበት ችግር አኳያ በአንፃራዊነት የተሻለ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ቢገኝም አሁንም የፊት ጥምረቱ ጥንካሬ ወደ የሚፈለገው ደረጃ ደርሷል ብሎ ለመናገር ግን አያስደፍርም።
ነገም የቀደመው የመከላከል ጥንካሬ ከማስቀጠል በዘለለ የጨዋታውን መንፈስ መቀየር የሚያስችሉ ቅፅበቶችን የመጠቀም ብቃታቸው በውጤት ደረጃ አንዳች ነገር ይዘው ከመውጣታቸው ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ይመስላል።
ወላይታ ድቻዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን 14 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ፋሲል ከነማዎች ሰባት ጊዜ ድል አድርገው 16 ግቦች ሲያስቆጥሩ 14 ግቦች ያሏቸው ወላይታ ድቻዎች አምስት ጊዜ አሸንፈዋል፤ ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
ስሑል ሽረ ከ ባህርዳር ከተማ
ስሑል ሽረ እና ባህርዳር ከተማ የሚያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ መገባደኛ መርሃግብር የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ።
ከመጀመርያው ሳምንት ድል በኋላ ለአምስት ተከታታይ ሳምንታት ማሸነፍ ያልቻሉት ስሑል ሽረዎች ከተከታታይ የአቻ እና የሽንፈት ውጤት ለመላቀቅ ባህርዳር ከተማን ይገጥማሉ።
ስሑል ሽረዎች ድል ማድረግ ባልቻሉባቸው አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥቦች አራት ነጥቦች ብቻ በማሳካት በድምሩ ሰባት ነጥቦች ሰብስበዋል።
ቡድኑ በመጀመርያው ሳምንት መርሃግብር ሁለት ግቦች ካስተናገደ ወዲህ ባከናወናቸው ጨዋታዎች ከአንድ ግብ በላይ ባለማስተናገድ የመከላከል ጥንካሬው ማስቀጠሉ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም ጉልህ ግብ የማስቆጠር ድክመት ይታይበታል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በአማካይ 0.6 ግብ ማስቆጠሩም የዚህ ማሳያ ነው።
በነገው ጨዋታ ደግሞ በሊጉ አንድ ግብ ብቻ ካስተናገደው ኢትዮጵያ መድን ቀጥሎ ጥቂት ግቦች ያስተናገደውን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን እንደ መግጠማቸው የማጥቃት አጨዋወታቸውን የጥራት ደረጃ ከፍ አድርገው መቅረብ ግድ ይላቸዋል።
ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች አገግመው ድልና የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ባህርዳር ከተማዎች ጉልህ የወጥነት ችግር ይስተዋልባቸዋል።
ቡድኑ በመጀመርያዎቹ አምስት መርሃግብሮች በተከታታይ ነጥብ ለማስመዝገብ መቸገሩም ለወጥነት ችግር እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። የጣና ሞገዶቹ በሰባት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ያስተናገደ እና በቀላሉ ለጥቃት የማይጋለጥ ጠጣር የመከላከል ጥምረት ገንብተዋል። ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾቹን አጥቶ ጭምር የባለፈው ውድድር ዓመት የመከላከል ጥንካሬው ማስቀጠል ቢችልም የግብ ማስቆጠር ችግሩ ቡድኑ በወጥ አቋም እንዳይዘልቅ ምክንያት ሆኗል።
በነገው ጨዋታም ከተጋጣሚያቸው የፊት መስመር ጥንካሬ አንፃር ተከላካይ ክፍላቸው ይፈተናል ተብሎ ባይገመትም ከስሑል ሽረ የተከላካይ ክፍል የሚጠብቃቸውን ፈተና የሚያልፉበት መንገድ የጨዋታውን መልክ ይወስነዋል።
ስሑል ሽረዎች ሀብታሙ ገዛኸኝ፣ አሌክስ ኪታታ፣ ሱሌይማን መሐመድ እና ክፍሎም ገብረህይወት በጉዳት ኤልያስ አሕመድ ደግሞ በቤተሰብ ችግር ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው። ኬቨን አርጊዲ እና ዐወት በሪሁ ደግሞ ከጉዳት አገግመው ልምምድ ቢጀምሩም በነገው ጨዋታ የመሰለፋቸው ጉዳይ አጣራጣሪ ነው። በባህር ዳር ከተማ በኩል ግን ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ ሁለት ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ አንድ አንድ ጨዋታ ተሸናንፈዋል። ባህርዳር ከተማ 2 ግቦች ስያስቆጥር ስሑል ሽረ 1 አስቆጥሯል።