ሪፖርት | የጦና ንቦቹ እና ዐፄዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል

የወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በሁለቱም አጋማሾች በተቆጠሩ ጎሎች 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ወላይታ ድቻዎች ከባህር ዳር ጋር ያለ ጎል ካጠናቀቀው ቡድናቸው ብዙዓየሁ ሰይፉን በቴዎድሮስ ታፈሠ ብቻ ሲቀይሩ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተረተው በነበሩት ፋሲል ከነማዎች በኩል ግን የአምስት ተጫዋቾች ቅያሪ ተደርጓል። ዮናታን ፍሰሃ ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ ጃቢር ሙሉ ፣ ዳግም አወቀ እና ቃልኪዳን ዘላለም አርፈው እዮብ ማቲያስ ፣ ብሩክ አማኑኤል ፣ ኤፍሬም ኃይሉ ፣ ቢኒያም ላንቃሞ እና አንዋር ሙራድ በቋሚነት ገብተዋል።

በፌዴራል ዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ መሪነት በጀመረው ከአቻ እና ሽንፈት የመጡ ቡድኖችን ያገናኘው መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ልቀው የተገኙት ወላይታ ድቻዎች 5ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ጥቃት የሰነዘሩት ከተከላካይ ጀርባ ኳስ የደረሰው መሳይ ሠለሞን በጥልቀት ገብቶ የሞከራት ሙከራ በግብ ጠባቂው ኦማስ ኦባሶጊ ብቃት የመከነች ሲሆን በሙከራዋም የፋሲሉ የግብ ዘብ ኦማስ ጉዳት በማስተናገዱ ለሰባት ያህል ደቂቃዎች ጨዋታው ሊቋረጥ ተገዷል።

ጨዋታው ሲቀጥል ከራሳቸው ሜዳ ኳስን ለማደራጀት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት በተጋጣሚያቸው በድግግሞሽ በመነጠቅ  ለጥቃት ተጋላጭ ሆነው የታዩት ፋሲሎች አጥቂዎቻቸውን ባማከሉ ተሻጋሪ ኳሶች ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ በተስተዋሉት የጦና ንቦቹ 26ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። ናትናኤል ናሴሮ በረጅሙ ያሻገረውን እና ካርሎስ ዳምጠው ጨርፎ የሰጠውን ኳስ ከግራ ወደ ሳጥኑ ገፋ አድርጎ የገባው መሳይ ሠለሞን አክርሮ መቶ በግብ ጠባቂው ኦማስ ስትመለስ ጥድፊያ ውስጥ የነበረው ተከላካዩ ኢዮብ ማቲያስ በራሱ መረብ ላይ ኳሷን አሳርፎ ድቻን መሪ አድርጓል።

ጎል ካስቆጠሩ በኋላ መጠነኛ መነቃቃት የነበራቸው ድቻዎች ጨዋታው ሊገባደድ በተቃረበበት ወቅት ግን በአፄዎቹ ሁለት ተከታታይ ሙከራዎች ተደርጎባቸዋል። ቢኒያም ላንቃሞ ከግራ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ከጎሉ ሁለት ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ ኳስን ያገኘው አንዋር ሙራድ ቢመታትም በግቡ ቋሚ ብረት እና በተከላካዮች ርብርብ አጋጣሚዋ መክናለች። በጭማሪው የአጋማሹ ደቂቃ በረከት ግዛው የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ሳጥን ውስጥ ይዞ የገባትን ኳስ አቻ አደረገ ተብሎ ቢጠበቅም በሚያስቆጭ መልኩ ኳሷን ወደ ውጪ ሰዷታል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ፋሲሎች የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ ገብተዋል። ጉዳት የገጠመው አንዋር ሙራድን ጨምሮ ኤፍሬም ኃይሉ እና ቢኒያም ላንቃሞን በማስወጣት ማርቲን ኪዛ ፣ ኪሩቤል ዳኜ እና ጃቢር ሙሉ ተተክተዋል። በአዳዲስ የተጫዋች ኃይል ዳግም ከተመለሱ በኋላ በይበልጥ መሻሻሎች የነበራቸው ፋሲሎች የእንቅስቃሴ የበላይነትን በመያዝ በአመዛኙ የተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ መገኘት ቢችሉም እንደነበራቸው ብልጫ ግን የድቻን የመከላከል አጥር በቀላሉ ሰብሮ ለመግባት ከብዷቸው ታይቷል።

ቃልኪዳን ዘላለምን በማስገባት የማጥቃት አማራጫቸው ዕድሳት ያደረጉት ፋሲሎች ከመጠነኛ የመልሶ ማጥቃት ውጪ በአመዛኙ ወደ መከላከል ያመዘኑትን የወላይታ ድቻን መዋቅር ማለፍ ተስኗቸው ለረጅም ደቂቃዎች ቢቆዩም 83ኛው ደቂቃ ላይ ግን ተቀይሮ የገባው ቃልኪዳን ዘላለም አሻምቶ ምኞት መቷት በግቡ ብረት ስትመለስ እግሩ ስር የገባችለትን ማርቲን ኪዛ በቀላሉ ወደ ጎልነት በመቀየር ጨዋታው በመጨረሻም 1ለ1 ተጠናቋል።