ሪፖርት| የጣና ሞገዶቹ ዳግም ወደ ድል ተመልሰዋል

የወንድወሰን በለጠ ሁለት ግቦች ባህርዳር ከተማን አሸናፊ አድርገዋል።


ስሑል ሽረዎች ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ አሰላለፍ ኤልያስ አሕመድ እና አሌክስ ኪታታ በዊልያም ሰለሞን እና አዲስ ግርማ ተክተው ሲገቡ ባህርዳር ከተማዎችም ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ ቡድን መሳይ አገኘሁ እና ጄሮም ፊሊፕ በፀጋዬ አበራ እና ሙጂብ ቃሲም ተክተው ገብተዋል።

በጥሩ እንቅስቃሴ እና ተመጣጣኝ ፉክክር የጀመረው ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች በሚታወቁበት የመስመር አጨዋወት ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ባህርዳር ከተማዎች የጠሩ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የተሻሉ ነበሩ። በሂደት ጫና በመፍጠር ብልጫውን መውሰድ የቻሉት የጣና ሞገዶቹ በአጋማሹ ሙጂብ ቃሲም በሁለት አጋጣሚዎች ባደረጋቸው እንዲሁም ፍፁም ዓለሙ ከሙጂብ ጋር በጥሩ ቅብብል ወደ ሳጥን ይዞት ገብቶ ግብ ጠባቂውን ጭምር በማለፍ ወደ ጎልነት ባልቀየረው ወርቃማ ዕድል ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። በተለይም ሙጂብ ቃሲም በአስራ ስምንተኛው ደቂቃ ላይ ከፍሬው ሰለሞን የተሻገረችለትና ወደ ግብነት ያልቀየራት ኳስ የጣና ሞገዶቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

በአጋማሹ በመስመር እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ብርሀኑ አዳሙ ከተከላካዮች በረዥሙ የተሻገረችለትን ኳስ የግብ ጠባቂውን መውጣት አይቶ በረዥሙ ባደረጋት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።

በመጀመርያው አጋማሽ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች ያመከኑት ባህርዳር ከተማዎች ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በደቂቃዎች ውስጥ በወንድወሰን በለጠ አማካኝነት ባስቆጠሯት ግብ ጨዋታውን መምራት ችለዋል። ፍሬው ሰለሞን ከተከላካዮች ጀርባ በረዥሙ የተሻገረለትን ኳስ ለሙጂብ ቃሲም አቀብሎት አጥቂው መቶ ግብ ጠባቂው ሞየስ ፖዎቲ ሲመልሰው በግቡ አፋፍ የነበረው ወንድወሰን በግንባር በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ያደረገው።

ከግቡ መቆጠር በኋላ በስሑል ሽረዎች በኩል ዊልያም ሰለሞን ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቶ የግቡን አግዳሚ በመለሰበት ኳስ አቻ ለመሆን ቢቃረቡም ከደቂቃዎች በኋላ ባህርዳር ከተማዎች በወንድወሰን በለጠ አማካኝነት መሪነታቸውን ያጠናከሩበት ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዕለቱ ሁለተኛዋን ግቡን ያስቆጠረው ተጫዋቹ ከሙጂብ ቃሲም በጥሩ መንገድ የተሻገረችለትን ኳስ ከተከላካዮች መሀል ሆኖ በግሩም መንገድ በማስቆጠር ነበር የቡድኑን መሪነት ያጠናከረው።

ጨዋታው ተጨማሪ ሙከራዎች ሳያስተናግድ መጠናቀቁን ተከትሎ በወንድወሰን በለጠ ሁለት ግቦች ታግዘው ያሸነፉት ባህርዳር ከተማዎች ነጥባቸው አስራ ሦስት በማድረስ ደረጃቸውን አሻሽለዋል።