ሀብታሙ ተከስተ ከዓመታት በኋላ ወደ ሜዳ ሊመለስ ነው

የፋሲል ከነማው አማካይ ሀብታሙ ተከስተ ከረጅም ወራት በኋላ ወደ ሜዳ ለመመለስ መቃረቡን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል።


በዳሽን ቢራ ተስፋ ቡድን የእግርኳስ ህይወቱን በመጀመር ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሀን በኋላም በ2009 መቐለ ከተማ በማምራት ቡድኑ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያድግ ትልቅ አስተዋፆኦ ያደረገው ሀብታሙ በፕሪሚየር ሊጉ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማድረግ ከ2011 ጀምሮ ዐፄዎቹን በመቀላቀቀል በክለቡም ሆነ በብሔራዊ ቡድን እጅግ የተሳኩ ዓመታትን አሳልፏል። ሆኖም ግን ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ያለፉትን 36 ወራት ከሜዳ በመራቅ ለፋሲል ከነማ ግልጋሎት ሳይሰጥ ቆይቷል።

ተጫዋቹ አሁን ቡድኑን በመቀላቀል ልምምድ መስራት የጀመረ ሲሆን በትላትናው ዕለትም ቡድኑ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ በስታዲየም በመገኘት የቡድኑን ጨዋታ ለመከታተል ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ የነበራቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሀብታሙ ተከስተ ወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ

“ ሀብታሙ በዚህ ቡድን ላይ ትልቅ ታሪክ ያለው ተጫዋች ነው። ለረጅም ጊዜ በጉዳት አልነበረም። ክረምት ነበር ሊቀላቀለን አስቦ የነበረው ከጤናው ጋር ተያይዞ ሊቀላቀለን አልቻለም። አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ ማገገሙን ተከትሎ ከእኛ ጋር እየሰራ ይገኛል።” በማለት ተናግረዋል።