የ9ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን በተከታዩ መሰናዷችን ይዘንላችሁ ቀርበናል።
አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በሽንፈት ሳምንቱን አጠናቀው የነበሩ ሁለት ቡድኖችን ከቀትር መልስ የሚያገናኘውን ጨዋታ በቅድሚያ የምንመለከተው ይሆናል።
የሊጉን የመክፈቻ ጨዋታ በስሑል ሽረ ገጥሟቸው ከነበረው ሽንፈት በኋላ በተከታታይ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ላይ ከሽንፈት ርቀው የነበሩት አዳማ ከተማዎች ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች በመቻል እና መድን ከተረቱበት ተከታታይ ሽንፈት ቀና ለማለት ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናግዳሉ። እስከ አሁን በከወኗቸው ሰባት ጨዋታዎች በሦስቱ ሽንፈት ፣ በሁለቱ ድል እና በሁለቱ ደግሞ አቻን በማስተናገድ በስምንት ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ 13ኛ ላይ መቀመጥ የቻሉ ሲሆን ወደ ላይ ፈቀቅ የሚያደርጋቸውን ድል እያለሙ ከሌላኛው የውጤት ናፋቂ ከሆነው ኢትዮጵያ ቡና ከባድ የሆነ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል። በይበልጥ ከመስመር የሚነሱ ማጥቃቶችን በጥልቅ የጨዋታ መንገድ የሚጠቀመው የአሰልጣኝ አብዲ ቡሊው ቡድን ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሰባት ያህል ጎሎችን በተጋጣሚው መረብ ላይ ቢያስቆጥርም በአንፃሩ በመከላከሉ ላይ ዘጠኝ ግቦችን ማስተናገዱ የኋላ ክፍሉ ላይ ከፍ ያለ መሻሻል እንደሚያስፈልገው ይህ ቁጥር ማሳያ ነው።
ከተጋጣሚያቸው በዕኩል የማሸነፍ ፣ የመሸነፍ እና የአቻ ውጤት እንዲሁም ተመሳሳይ ስምንት ነጥብን በመያዝ አስራ አንደኛ ቦታ ላይ በደረጃ ሰንጠረዡ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከሀዲያ ሆሳዕናው ሽንፈት ለማገገም ከአዳማ ከተማ ጋር ይጫወታሉ። ከሽንፈት ወደ ድል በተመለሱበት የመቐለው ጨዋታ ላይ በብዙ የማጥቃት ፍላጎቶች ልቀው የተገኙት ቡናማዎቹ ባሳለፍነው ሳምንት ግን በሀዲያ ሆሳዕና 1ለ0 ሲረቱ መጠነኛ መቀዛቀዞችን ዐሳይተዋል። ሰባት ጎል አስቆጥረው በተቃራኒው ደግሞ ሰባት ጎሎች መረባቸው ላይ ያረፉባቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ውጤታማ ያደረጋቸውን ወደ መስመር ያዘነበለውን የማጥቃት አደረጃጀት መልሰው የማያገኙ ከሆነ ነገ የሚገጥሙት በተመሳሳይ መስመሮችን በይበልጥ የሚጠቀመው አዳማ ከተማን እንደመግጠማቸው ጥንቃቄዎች በደንብ ሊያስፈልጓቸው እንደሚችሉ መናገር ይቻላል።
በአዳማ ከተማ በኩል የግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ በጉዳት መድረሱ ሲያጠራጥር አማካዩ ዳንኤል ደምሱ ግን አሁንም አይኖርም። ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው የበፍቃዱ ዓለማየሁ እና መላኩ አየለን ግልጋሎት አሁንም የማያገኙ ይሆናል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 44 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 23 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አዳማ ከተማ በበኩሉ 9 ጊዜ ድል ሲቀናው በ12 ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 76 ፤ አዳማ 40 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።
አርባምንጭ ከተማ ከ መቻል
የሊጉን መሪ ወገብ ላይ ከሚገኘው ክለብ ጋር የሚያገናኘው ጨዋታ ምሽት ላይ ይደረጋል።
በሰባት ጨዋታዎች ሦስት ድል ፣ ሦስት ሽንፈት እና የአንድ የአቻ ውጤትን በመያዝ በሰንጠረዡ አስረኛ ላይ መቀመጥ የቻለው የአሰልጣኝ በረከት ደሙው አርባምንጭ ከተማ በአራት ነጥብ ብቻ ከበለጠው እና ሊጉን እየመራ ካለው ጠንካራው መቻል ጋር ጨዋታውን ያደርጋል። በሊጉ ላይ የወጥነት ችግር ከሚስተዋልባቸው እና ለመገመት አዳጋች ከሆኑ ቡድኖች ውስጥ የሚመደቡት አርባምንጭ ከተማዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰባቸው ሽንፈት ያገገሙበትን ባለፈው ሳምንት በወልዋሎ ላይ በተቀናጁት ድል ዕፎይ ማለት የቻሉ ሲሆን የቆሙበት ድል ቀጣይነት እንዲኖረው ነገም በብርቱ ይታገላሉ። ስድስት ግቦችን ቢያስቆጥሩም በተቃራኒው ተመሳሳይ የሆነ የግብ መጠንን ያስተናገዱት አዞዎቹ መጠነኛ ክፍተት ከሚስተዋልበት የመሐል ሜዳቸው በተጨማሪ በሁለቱም የፊት እና የኋላ ክፍል ላይ ዕርምትን መውሰድ ይኖርባቸዋል በአንፃሩ ለኳስ ቁጥጥሩ ቅድሚያ የሚሰጠውን መቻልን እንደመግጠማቸው ጥንቃቄዎች ላይ ይበልጥ ትኩረት መስጠታቸው የሚቀር አይመስልም።
አራት ጨዋታዎችን አሸንፈው ሁለት የአቻ እና አንድ ሽንፈት ደግሞ ገጥሟቸው የሊጉ አናት ላይ በአስራ አራት ነጥቦች የተቀመጡት መቻሎች የነጥብ ልዩነቱን ለማስፋት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ይጫወታሉ። በሲዳማ ቡና በሁለተኛው የጨዋታ ሳምንት ከደረሰባቸው ሽንፈት በስተቀር እስከ አሁን ሙሉ ሦስት ነጥብን ለተጋጣሚዎቻቸው ያልሰጡት መቻሎች ከጨዋታ ጨዋታ እያሳደጉ የመጡትን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በነገው ዕለትም እንደሚያስቀጥሉ ይታመናል። ከአማካይ ክፍሉ መነሻ በሚሆኑ የንክኪ ኳሶች ወደ መስመር በማድላት በደንብ ሲያጠቁ የሚስተዋሉ መቻሎች ባለፈው ሳምንት ከኤሌክትሪክ ጋር በነበራቸው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ አቀራረባቸው ዝግ ከማለቱ ባለፈ ደከም ብሎ የታየ ሲሆን ይህንን ክፍተት ማስተካከል ትልቁ የቤት ሥራቸው ይሆናል ይህንን ቀርፈው የማይገኙ ከሆነ ግን ለተጋጣሚያቸው ፈጣን ሽግግር መጋለጣቸው የማይቀር ይሆናል።
አርባምንጮች አበበ ጥላሁን እና ቻርለስ ሪባኑን በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲያደርጉ የይሁን እንዳሻው የመሰለፍ ጉዳይ ግን አጠራጣሪ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ18 ጊዜያት ያህል የተገናኙ ሲሆን አርባምንጭ ከተማ 6 መቻል በአንፃሩ 5 ጨዋታዎችን አሸንፏል። ፣ በቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ነጥብ ሲጋሩ አዞዎቹ 15 መቻሎች በበኩላቸው 13 ጎሎችን በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።