የዕለቱ ቀዳሚ በነበረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ1 በመርታት ወሳኝ ድልን አሳክቷል።
በኢትዮጵያ መድን በመጨረሻ ጨዋታ ሽንፈት ካስተናገደው ቡድን ውስጥ አዳማ ከተማዎች የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ናትናኤል ተፈራ ፣ ፍቅሩ ዓለማየሁ እና ሱራፌል ዓወል አርፈው በዳግም ተፈራ ፣ ፉዓድ ኢብራሂም እና ነቢል ኑሪ ሲተኩ በሀድያ ሆሳዕና በጠባብ ውጤት ተሸንፈው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ዳዊት ሽፈራውን በዋሳዋ ጂኦፎሪ ፣ አማኑኤል አድማሱን በኮንኮኒ ሀፊዝ ቦታ በመተካት ገብተዋል።
ለ45ኛ ጊዜ ሁለቱን ቡድኖች ያገናኘው ጨዋታ ጎልን ያስመለከተን ገና በ25ኛው ሰከንድ ነበር ፤ አሜ መሐመድ ከቀኝ የሜዳው ክፍል ላይ ሆኖ ከአማካይ ክፍሉ የተቀበለውን ከተከላካዮች ቀድሞ ነፃ ቦታ ለተገኘው ስንታየሁ መንግሥቱ የሰነጠቀለትን ኳስ ቁመታሙ አጥቂ በድንቅ አጨራረስ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት አዳማን መሪ ያደረገች ግብን መረብ ላይ አሳርፏል።
ግብ ካስተናገዱ በኋላ ፈጠን ባሉ ሽግግሮች ብልጫውን በመያዝ ቶሎ ቶሎ የተጋጣሚያቸው ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ላይ ይገኙ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች እንዳሳዩት ብልጫ ወደ አቻነት የሚመልሳቸው ግብ ለማስቆጠር የነበራቸው ጥረት ግን ውስንነቶች ቢታይበትም ራሳቸው አዳማዎች በሰሩት ስህተት ወደ ጨዋታ የመለሳቸውን ግብ አግኝተዋል።
15ኛው ደቂቃ የአዳማ ከተማው የግብ ዘብ ዳግም ተፈራ ወደ ኋላ ከአማካይ ክፍሉ የደረሰውን ኳስ በአግባቡ ማፅዳት ባለመቻሉ ከአጠገቡ የነበረው ኮንኮኒ ሀፊዝ ጫና አክሎበት አንተነህ ተፈራ ደርሶ በማስቆጥር ጨዋታው ወደ 1ለ1 ተሸጋግሯል።
በእንቅስቃሴ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በመልሶ ማጥቃት ከመስመር አሜ መሐመድን ባማከለ መልኩ ቡናዎች ትተው የሚሄዱትን ክፍት ቦታ ሲጠቀሙ አደገኛ መሆናቸውን ያሳዩት አዳማዎች 27ኛው ደቂቃ አሸናፊ ኤልያስ ከቀኝ ወደ ውስጥ ያሻገረው ኳስን ስንታየሁ መንግሥቱ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛዋን ግብ አክሏል።
ተመጣጣኝ ፉክክርን ነገር ግን የኢትዮጵያ ቡና መጠነኛ የበላይነትን በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ማየት ብንችልም አጋማሹ በአዳማ የ2ለ1 ውጤት ተገባዷል።
ከመጀመሪያው አንፃር መጠነኛ መቀዛቀዝ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በይበልጥ ቡናማዎች ከደቂቃ ደቂቃ በሁሉም ረገድ የበላይነትን የወሰዱበት ነበር።
የተጫዋች ቅያሪን ጭምር በማድረግ በቅብብሎች እና ከቆሙ ኳሶች በድግግሞሽ ሦስተኛው የማጥቂያ ሜዳ ላይ ረጅሙን ደቂቃ ቡናማዎቹ ቢያሳልፉም ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሻሽሎ የተገኘውን የግብ ዘቡ ዳግም ተፈራን መረብ አልፎ ማስቆጠር ቀላል አልሆነላቸውም።
58ኛው ደቂቃ ከቀኝ ሳጥኑ ጠርዝ ተቀይሮ የገባው አማኑኤል አድማሱ አክርሮ መቶ ዳግም ያመከነበት እና በተከታታይም ከሳጥን ውጪ እና ከቆሙ ኳሶች አንተነህ እና ኮንኮኒ ያደረጓቸውን ከባድ ሙከራዎች በግቡ ዘቡ የነቃ ተሳትፎ ከጎልነት የተረፉት አጋጣሚዎች ተጠቃሾቹ ናቸው።
የኋላ ክፍላቸው ላይ ጥንቃቄ ወስደው ነገር ግን የሚያገኟቸውን ጥቂት ኳሶች በመልሶ ማጥቃት መጫወትን መርጠው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት አዳማ ከተማዎች ነቢል ኑሪ እና አሜ ካመከኗቸው ሁለት ድንገተኛ ሙከራዎች በስተቀር በርካታ የጎል ማግባት ጥቃቶች በተጋጣሚያቸው ቢደርስባቸውም በመከላከሉ ያሳዩን ጠጣር አቋሞ በመጨረሻም ጨዋታውን 2ለ1 አሸንፈው እንዲወጡ አስችሏቸዋል።