በ9ኛው ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን የሚካሄዱ መርሃግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ሲዳማ ቡና ከ ፋሲል ከነማ
በመጨረሻው ጨዋታ ከሽንፈት መልስ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት እና ከራቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ወደ ሜዳ የሚገቡትን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር ነው።
ከተከታታይ አራት ድሎች በኋላ በባህርዳር ከተማ ሽንፈት ገጥሟቸው በመጨረሻው መርሃግብር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ተጋርተው የወጡት ሲዳማ ቡናዎች ከመሪዎቹ ተርታ ላለመራቅ ዳግም ወደ አሸናፊነት መመለስ ይጠበቅባቸዋል።
ሲዳማ ቡናዎች በሊጉ ከኢትዮጵያ መድን እና ባህርዳር ከተማ በመቀጠል ጥቂት ግቦች ያስተናገደና ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት እንዳላቸው ማስመስከር ቢችሉም የማጥቃት ጥንካሬያቸው ከጨዋታ ጨዋታ እየተዳከመ ይገኛል። ቡድኑ በጥራትም ይሁን በጥልቀት የላቀ የፊት መስመር ጥምረት ቢኖረውም በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ጉዞ እያደረገ አይገኝም። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነው ጥምረት ላይ ውስን ማስተካከያዎች ማድረግም የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቀዳሚ ስራ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚ በተጨማሪ በመጨረሻው ጨዋታ ከመስፍን ታፈሰ ወደ ሳጥን በሚሻገሩ ኳሶች የተሻሉ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የሞከረው ቡድኑ ግቦችን ለማስቆጠር ተጨማሪ ዕድሎችን የመፍጠርያ መንገድ ማበጀት ይኖርበታል።
ከድል ጋር ከተራራቁ ሰባት ጨዋታዎች ያስቆጠሩት ዐፄዎቹ በስምንት ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
እንደ ወትሮ የላቀ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ማስመዝገብም ይሁን ጨዋታዎች በመቆጣጠር ረገድ ድክመቶች የተስተዋለባቸው ዐፄዎቹ ከተከታታይ ሽንፈቶች በማገገም ነጥብ መጋራታቸው እንደ አወንታ የሚነሳላቸው ነጥብ ቢሆንም በዋነኝነት በጨዋታዎች ውስጥ ያላቸው የወጥነት ችግር መቅረፍ ግድ ይላቸዋል። ቡድኑ በመጨረሻው መርሀ-ግብር ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በብዙ ረገድ የተሻሻለ ብቃት ማሳየታቸው በነገው ጨዋታ ተሻሽለው መቅረብ እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጠ ቢሆንም ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ አንፃር ቀላል ፈተና እንደማይጠብቃቸው ግን እሙን ነው።
እንደ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ገለፃ ከሆነ ከውጤት ጋር ተያይዞ ጫና ውስጥ ላሉት የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ያሳኩት አንድ ነጥብ በስነ-ልቦና ደረጃ ዋጋው ትልቅ ነው።
ቡድኑ የመጨረሻውን ጨዋታ የጀመረበት አኳኋን ጥሩ ያልነበረ ቢሆንም በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ባደረጋቸው ለውጦች ብልጫ የወሰደበት መንገድ በነገ አቀራረቡ ላይ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።
በጥቅሉ ቡድኑ ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ ከነበረበት ጫና አንፃር ከነጥቡ ባሻገር እንቅስቃሴው ላይ ውስን መሻሻል መታየቱ ከነገው ዓይነት ጠንከር ያለ ፍልሚያ በፊት የሚኖረውን የሥነ ልቦና ጠቀሜታ ከፍ ያለ እንደሆነም ይታመናል።
በሲዳማ ቡና በኩል ሁሉም ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
በሊጉ 14 ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ፋሲል ከነማ ስምንት ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ሲዳማ ቡናዎች አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ችለዋል፤ አንድ ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ፋሲል ከነማ 22 ግቦች ሲያስቆጥር ሲዳማ ቡና ደግሞ 16 አስቆጥሯል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)
መቐለ 70 እንደርታ ከ ባህርዳር ከተማ
በተለያየ የውጤት መንገድ ያሉት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ምዓም አናብስት ወደ ድል ለመመለስ የጣና ሞገዶቹ ደግሞ ድላቸውን ለማስቀጠል ከአራት ዓመታት በኋላ ያገናኛል።
በአራት መርሀ-ግብሮች ሁለት ድል እና ሁለት የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ሽንፈት ሳይቀምሱ ከዘለቁ በኋላ ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ያስተናገዱት ምዓም አናብስት ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ከጣና ሞገዶቹ ጋር ይፋለማሉ።
በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ታልሞ የተገነባ የሚመስለው የመቐለ 70 እንደርታ ስብስብ በመጀመርያዎቹ መርሀ-ግብሮች አጨዋወቱን በተሻለ መንገድ መተግበር ቢችልም በቅርብ ጨዋታዎች በሁሉም ረገድ ተዳክሞ ተከታታይ ጨዋታዎች ለመሸነፍ ተገዷል። በተለይም ከጨዋታ ጨዋታ ይበልጥ ተጋላጭ እየሆነ የመጣው ጉልህ የመከላከል አደረጃጀት ድክመት የቡድኑ ዋነኛ ደካማ ጎን ነው። ጥምረቱ በመጀመርያዎቹ አራት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ በማስተናገድ በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችልም ቀጥለው በተካሄዱ ሦስት መርሀ-ግብሮች ግን ስምንት ግቦች ማስተናገድ ችሏል።
በተደጋጋሚ ጉዳት እና ቅጣት ምክንያት ወጥነት ያለው የተጫዋቾች ምርጫ ማድረግ ያልቻሉት አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ የመከላከል አደረጃጀታቸው ላይ ማስተካከያዎች ማድረግ ቀዳሚ ስራቸው ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም ከትኩረት ማነስ እና በደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር የሚመጡ ግለ-ሰባዊ ስህተቶች መቀነስም ሌላው ማስተካከል የሚጠበቅባቸው ክፍተት ነው። ቡድኑ ሊጉ ከተጀመረ ወዲህ አንድ ወደ ራስ የተቆጠረ ግብ ጨምሮ አራት የፍፁም ቅጣት ምቶች ማስተናገዱም የችግሩ ሁነኛ ማሳያ ነው።
ከዚ በተጨማሪ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ለነገው ተጋጣሚው ባህርዳር ከተማ አሁናዊ የመከላከል ብቃት ከግምት ውስጥ ያስገባ አቀራረብ ማበጀት ይጠበቅበታል። ባህርዳር ከተማ በሊጉ ዝቅተኛ የግብ መጠን በማስተናገድ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ ጠጣር አደረጃጀት ያለው ቡድን መሆኑ ሲታሰብ ግን ፈተናው ቀላል እንደማይሆን መገመት ይቻላል።
ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች በማገገም በሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦች በመሰብሰብ 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የጣና ሞገዶቹ ከመሪዎቹ ጎራ ላለመራቅ ሦስት ነጥብ አስፈላጊያቸው ነው።
ባህርዳር ከተማዎች እስከ ቅርብ ሳምንታት የነበረባቸው የወጥነት ችግር ቀርፈዋል። ቡድኑ
በመጀመርያዎቹ አምስት ጨዋታዎች በድል እና በሽንፈት መሀል እየዋለለ ተከታታይ ነጥቦች ማስመዝገብ ቢሳነውም በመጨረሻዎቹ ሦስት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች ግን ሰባት ነጥቦች በማስመዝገብ ሲዋዥቅ የነበረው ብቃቱ አርሟል።
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው አሁንም ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት ጠንካራ፣ በቀላሉ ለጥቃት የማይጋለጥ እና የተረጋጋ የመከላከል አደረጃጀት ገንብተዋል። በውጤቱም ቡድኑ በጨዋታ በአማካይ ከግማሽ በታች (0.3) ግቦች ከማስተናገዱም በተጨማሪ በአምስት መርሀ-ግብሮች መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። ከዚ በተጨማሪም በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች አጥጋቢ ያልነበረው የማጥቃት አጨዋወቱ በሂደት ወደ ጥሩ ብቃት በመምጣት በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦች በማስቆጠር ለቡድኑ ውጤት ማማር የበኩሉን ተወጥቷል። ቡድኑ አሁንም ጨዋታ ቀያሪ የግብ ዕድሎች እየፈጠረ መቀጠሉ በጥሩነት የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም የሚስተዋሉት ውስን የአፈፃፀም ችግሮች መቅረፍ ይጠበቅበታል።
በጉዳት እየታመሱ የሚገኙት መቐለ 70 እንደርታዎች በነገው ጨዋታ ኮከብ ግብ አስቆጣሪው ያሬድ ብርሀኑን ጨምሮ
ተከላካዮቹ መናፍ ዐወል እና ዮናስ ግርማይ እንዲሁም ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ፣ ቤንጃሚን አፉቲ እና ዓወት ኪዳኑ በጉዳት አያሰልፉም። ባህርዳር ከተማዎች ግን በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
ሁለቱ ቡድኖች ከተሰረዙት ሁለት የ2012 የውድድር ዓመት ጨዋታዎች ውጭ በፕሪምየር ሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጨዋታዎች ሲሸናነፉ በተመሳሳይ አንድ አንድ ግቦችን አስቆጥረዋል።