የበረከት ግዛው ብቸኛ ግብ ከሳምንታት ጥበቃ በኋላ ፋሲል እና ድልን አስታርቃለች።
ሲዳማ ቡናዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ 11 ፍራኦል መንግስቱ፣ አማኑኤል ላርዬ፣ ብርሀኑ በቀለ እና መስፍን ታፈሰን በጊት ጋትኩት፣ ሬድዋን ናስር፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ማይክል ኪፕሩቪ ተክተው ሲገቡ ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ከተጋራው ቋሚ 11 ኦማስ ኦቦሶጊ፣ ብሩክ አማኑኤል፣ ኤፍሬም ኃይሉ፣ አንዋር ሙራድ እና ቢንያም ላንቃሞ በዮሐንስ ደርሶ፣ ኪሩቤል ዳኜ፣ ቃልኪዳን ዘላለም፣ ጃቢር ሙሉ እና ማርቲን ኪዛ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ብዙም ማራኪ እንቅስቃሴ ያልታየበት እና ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ ፉክክር ያደረጉበት የመጀመርያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረገበት ነበር። ቡድኖቹ በሁሉም ረገድ ተቀራራቢ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ግን ሲዳማ ቡናዎች በአንፃራዊነት የተሻሉ ነበሩ።
ማይክል ኪፕሩቪ በተከላካይ ስህተት ያገኛትን ኳስ ለሳሙኤል ሳሊሶ አቀብሎት የመስመር ተጫዋቹ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ መቷት ዮሐንስ ደርሶ ያዳናት ኳስም ሲዳማን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረ።
ቡድኑ ከተጠቀሰች ሙከራ ውጭም ደስታ ደሙ አሻምቷት በሳጥኑ ውስጥ የነበረው ሀብታሙ ታደሰ አብርዶ መቷት ዮሐንስ ደርሶ በመለሳት ሙከራ ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥረዋል።
በዐፄዎቹ በኩልም ቃልኪዳን ዘላለም ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቷት ቶም ኢካራ የመለሳት ኳስ የተሻለ ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች።
በእንቅስቃሴም ይሁን በፉክክር ረገድ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎች ያስመለከተን ነበር። ማርቲን ኪዛ ከግቡ ቅርብ ርቀት አግኝቶ ሞክሯት ወደ ውጭ በመወጣችውና ቡድኑን ቀዳሚ ለማድረግ በተቃረበች ሙከራ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል መድረስ የጀመሩት ዐፄዎቹ በረከት ግዛው በአርባ ዘጠነኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።
አማካዩ አምበሉ ጌታነህ ከበደ ከቀኝ መስመር አሻምቷት ግብ ጠባቂው የጨረፋትን ኳስ በግንባር በማስቆጠር ነበር ቡድኑ መሪ ማድረግ የቻለው።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ፋሲሎች በአመዛኙ በመከላከል ላይ ያተኮሩ እንቅስቃሴ ስያደርጉ ሲዳማ ቡናዎች ግን የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት ጫና ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ደስታ ዮሐንስ በሁለት አጋጣሚዎች ከቆመ ኳስ ካደረጋቸው ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ውጭ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም፤ በተለይም ተከላካዩ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከግቡ በቅርብ ርቀት ያገኛትን የቆመች ኳስ መቶ ዮሐንስ ደርሶ ወደ ውጭ ያወጣት ቡድኑን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።
ጠንካራ ፉክክር ያስመለከተን ጨዋታ በፋሲል ከነማ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ዐፄዎቹ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቀዋል።