ፌዴሬሽኑ የአሰልጣኝ ዮሃንስን ስንብት ይፋ አድርጓል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን ኮንትራት ማቋረጡን ዛሬ ለሚድያ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እንዲሰናበቱ የተወሰነው ባለፈው ሳምንት ቢሆንም የአሰልጣኙን ጨምሮ የረዳቶቹን እና የቴክኒክ ኮሚቴው አባላት ስንብት ይፋ የተደረገው ዛሬ ነው፡፡

 

የፌዴሬሽኑ መግለጫ ይህንን ይመስላል፡-

የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ የሥራ ውል ከዛሬ ጀምሮ እንዲቋረጥ ተደረገ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ መካከል ሚያዚያ 23/2007 ዓ.ም የተፈረመው የሥራ ውል ከዛሬ ሚያዚያ 24 ቀን 2008 ዓ.ም በስምምነት እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

የሥራ ውሉ ከዛሬ ጀምሮ እንዲቋረጥ መደረጉን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ2017 ዓ.ም የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጋር በተያያዘ ለሚጠብቁት ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ኃላፊነት የሚወስደው አሰልጣኝ በፌዴሬሽኑ ኢመርጀንሲ ኮሚቴ አማካኝነት ተመርጧል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዚያ 19 ቀን 2008 ዓ.ም ያሳለፈውን የአሰልጣኝ የሰንብት ውሣኔ በጽህፈት ቤት አማካኝነት በህግና አስተዳደራዊ አግባብ መሠረት ፤ ከሥራ ውሉ አንፃር ታይቶ በስምምነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እልባት እንዲያገኝም ከአሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

“When you are torn between two always pick both” እንደሚባለው ሁሉ ከቴክኒክ ልማት ቋሚ ኮሚቴ በየጊዜው ወቅቱን የጠበቀ በቂ አመራር ባለመሰጠቱና ፌዴሬሽኑ ለአላስፈላጊ ውዝግብ በመዳረጉ፤ በአሰልጣኙ በኩልም የሚፈለገው ውጤት አለመምጣቱ ለሁለቱም አካላት ስንብት ምክንያት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከእዚሁ ጋር ተያይዞ አዲስ የተመረጠው አሰልጣኝ ማንነት ዝርዝር የሥራ ውል ሂደቱ እንደተጠናቀቀ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይፋ ይደረጋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *