ሪፖርት | ነብሮቹ ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን አሳክተዋል

ሀዲያ ሆሳዕና የ1ለ0 ውጤትን በተመሳሳይ በተከታታይ ሦስተኛ ጨዋታቸው ስሑል ሽረን በመርታት አስመዝግበዋል።

በባህር ዳር ከተማ በተጠናቀቀው የጨዋታ ሳምንት ሽንፈት ገጥሟቸው የነበሩት ስሑል ሽረዎች የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ነፃነት ገብረመድህን ፣ አዲስ ግርማ እና ፋሲል አስማማው አርፈው ክብሮም ብርሀነ ፣ ብሩክ ሀዱሽ እና አላዛር አድማሱ በቋሚ አሰላለፍ ሲተኩ ኢትዮጵያ ቡናን 1ለ0 አሸንፈው የነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ግን ምንም ቅያሪ ሳያስፈልጋቸው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ተመጣጣኝ የጨዋታ አቀራረቦችን ያስተዋልንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ወደ መስመር ያደሉ እንቅስቃሴዎች በይበልጥ የተደረጉበት ቢሆንም የግብ ዕድሎች ግን ብዙም ያልተፈጠሩበት ነበር። መጠነኛ ብልጫን በመጀመሪያው አምስት ደቂቃዎች ውስጥ የወሰዱ ይመስሉ የነበሩት ሽረዎች በአላዛር አድማሱ ከግራ በኩል በተደረገ በኋላም ያሬድ በቀለ ባወጣት አጋጣሚ ጥቃት በመሰንዘሩ ቀዳሚዎች ሆነዋል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በረጃጅም እና ወደ መስመር ባጋደሉ ኳሶች ግብን ለማስቆጠር ጥረቶች ያልተለዩዋቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደጋግመው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ መድረስ የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ጥራት ባለው ሙከራ ግን መታጀብ ሳይችል ቀርቷል። ከመጀመሪያዎቹ ሰላሳ ደቂቃዎች በኋላ እየተቀዛቀዘ በቀጠለው የቡድኖቹ ጨዋታ ሽረዎች 41ኛው ደቂቃ ላይ ደካማ እንቅስቃሴን ባደረገው ዊሊያም ሠለሞን ምትክ ፋሲል አስማማውን ቀይረው ከማስገባታቸው በስተቀር በጨዋታው በልዩነት ሊነሳ የሚችል ነገርን ሳናይበት ያለ ጎል ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት በተመለሰው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹን አስር ደቂቃዎች ወደ መስመር አጋድለው በተሻጋሪ ኳሶች ለመጫወት ስሑል ሽረዎች ጥረት ያደረጉበት እና በአንፃሩ ሀድያ ሆሳዕናዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመጣል ለማጥቃት ሲዳዱ ብንመለከትም ግልፅ የግብ ዕድሎች ተፈጥረው ያልተስተዋለበት ነበር።

በጎል ሙከራዎች አይድመቅ እንጂ በእንቅስቃሴ እየደመቀ ተመጣጥኖ በቀጠለው ጨዋታ የተጫዋች ቅያሪን ከ60 ደቂቃዎች በኋላ ሀድያ ሆሳዕናዎች ካደረጉ በኋላ ጨዋታውን ቀስ በቀስ እየተቆጣጠሩ መጥተው በተለይ የመጨረሻዎቹን ሀያ ደቂቃዎች በፈጠሩት ተደጋጋሚ ጫና ጎል አስቆጥረዋል። 77ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ በቡድን አጋሩ ተጨርፎ ያገኘው ብሩክ ማርቆስ በማስቆጠር ሀድያ ሆሳዕናን መሪ አድርጓል።

በተጋጣሚያቸው ግብ ካስተናገዱ በኋላ መጠነኛ መነቃቃት በስሑል ሽረዎች በኩል የተስተዋለ ቢሆንም ጨዋታው ሙከራዎችን ሳያሳየን በመጨረሻም ሀድያ ሆሳዕናን አሸናፊ በማድረግ ተቋጭቷል። ቡድኑም በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች በተመሳሳይ የ1ለ0 ድልን ማሳካት ችሏል።