መቐለ 70 እንደርታ ከጋናዊው ጋር በስምምነት ተለያይተዋል

ለዘጠኝ ደቂቃዎች ብቻ ቡድኑን ያገለገለው ቁመተ ሎጋ አጥቂ ከምዓም አናብስት ጋር የነበረው እህል ውሀ አብቅቷል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት መቐለ 70 እንደርታን ተቀላቅሎ ከቡድኑ ጋር የወራት ቆይታ ያደረገው ጋናዊው አጥቂ ኮፊ ኮርድዚ ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያየ። በውድድር ዓመቱ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በተደረገ ጨዋታ ብቻ ለዘጠኝ ደቂቃዎች ሜዳ ላይ የቆየው ይህ አንድ ሜትር ከሰማንያ አምስት ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ግዙፍ አጥቂ ምዓም አናብስትን በአንድ ዓመት ውል መቀላቀል ቢችልም በሚፈለገው ደረጃ ማገልገል ባለመቻሉ ክለቡን ለቋል።

ከሊቢያው ክለብ አልታሃዲ ቤንጋዚ ጋር የነበረውን ቆይታ ካጠናቀቀ በኋላ በመቐለ የወራት ቆይታ የነበረው ይህ የ30 ዓመት ተጫዋች ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች በኸርትስ ኦፍ ኦክ እንዲሁም በሌጎን ሲቲ እና በኳታር ሁለተኛ ዲቪዚዮን ተሳታፊ ክለብ ሙ አይተር መጫወቱ ይታወሳል።

በዘጠኝ ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች በቀጣይ ሐሙስ ከሀዋሳ ከተማ፤ በ11ኛው ሳምንት ደግሞ ከስሑል ሽረ ጋር ይጫወታሉ።