የ10ኛው ሳምንት መክፈቻ የሆኑ መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና
ሀዋሳ ከተማን ካሸነፈ በኋላ ሙሉ ብልጫ በወሰደበት የኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት የተገደደው ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ከገጠመው የውጤት ውጣ ውረድ ለመላቀቅ ወደ ሜዳ ይገባል።
ብርቱካናማዎቹ በመጨረሻው መርሐግብር በቅርብ ሳምንታት ካሳዩት የላቀ ብቃት ማሳየት ቢችሉም ደካማ የነበረው ዕድሎችን የመጠቀም ብቃታቸውን ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ አስችሏቸዋል። ቡድኑ ባለፉት ሳምንታት ከነበረው ውስን የማጥቃት ድክመቶች በቶሎ ተላቅቆ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በመከላከል ጥንካሬያቸው ቀዳሚ ከሆኑት ክለቦች አንዱ የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክን በዚህ ደረጃ መፈተኑ እንደ አንድ ጥሩ ጎን የሚነሳለት ቢሆንም ዓመቱን በጥሩ መንፈስ ጀምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአፈፃፀም ደረጃው በማሽቆልቆል ላይ ያለው የፊት ጥምረቱ ብቃት መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅበታል።
ቡድኑ በጨዋታዎች ካለው ብልጫ በዘለለ አሁንም ዕድሎች እየፈጠረ መቀጠሉ ትልቅ ግምት እንዲሰጠው የሚያደርግ ነጥብ ነው፤ ሆኖም የጨዋታ መልክ የሚቀይሩ ወርቃማ የግብ አጋጣሚዎች የመጠቀም ጉልህ ድክመቱን የማረም የቤት ሥራ ይጠብቀዋል።
በአስራ ሦስት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች በፋሲል ከነማ ከገጠማቸው ሽንፈት በቶሎ ለማገገም ከብርቱካናማዎቹ ጋር ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሲዳማ ቡናዎች ከአራት ተከታታይ ድሎች በኋላ ባከናወኗቸው ሦስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻሉም፤ ቡድኑ በጨዋታዎቹም ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥቦች አንዱን ብቻ በማሳካት በደካማ ወቅታዊ አቋም ከመገኘቱም በተጨማሪነት ላለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ተስኖታል። የተለያየ ‘ፕሮፋይል’ ባላቸው እንዲሁም በጥራትም ሆነ በጥልቀት የተሻለ የፊት መስመር የተጫዋቾች ምርጫ ያላቸው አሰልጣኝ ዘላለም ባለፉት ጨዋታዎች ከገጠማቸው የጎል ድርቅ ለመላቀቅ ተጨማሪ የግብ ዕድሎች መፍጠሪያ መንገድ ማበጀት ግድ ይላቸዋል። ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በተወሰነ መልኩ የተሻሻለ የማጥቃት አቅም ማሳየቱ ባይካድም በጥቅሉ ሲታይ ግን የፊት መስመር ተጫዋቾቹ በቂ ዕድሎች እየተፈጠረላቸው ነው ብሎ መናገር አይቻልም። እንደ አሰልጣኝ ዘላለም ገለፃ ቡድኑ ለዋንጫ የሚጫወት ከሆነ የማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ለውጦች ማድረግ ቀዳሚ ሥራው መሆን ይገባዋል።
ሲዳማ ቡናዎች በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ ድሬዳዋ ከተማዎችም በተመሳሳይ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች ባይኖርም መጠነኛ ጉዳት የገጠማቸው ያሬድ ታደሰ እና ሄኖክ ሐሰን የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።
ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና እስካሁን በሊጉ 22 ጊዜ ተገናኝተዋል። ከእነዚህ ግንኙነቶች ሲዳማ ቡና አስሩን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አራት ጊዜ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ ረቷል፤ ቀሪዎቹ ስምንት የእርስ በርስ ግንኙነቶች በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ነበሩ።
በጨዋታዎቹ ሲዳማ ቡና 24 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 14 ግቦችን አስቆጥረዋል።
መቻል ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው በርካታ የአቻ ውጤቶች ታሪክ ያላቸውን ሁለት የሸገር ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ምሽት ላይ ይደረጋል።
በአስራ ሰባት ነጥቦች በሰንጠረዡ አናት ላይ የተቀመጡት መቻሎች በመሪነቱ ለመቀጠል በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ካሉት ፈረሰኞቹ ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
በሊጉ የመጀመርያ ጨዋታቸው በሲዳማ ቡና ሽንፈት ካስተናገዱ ወዲህ ላለፉት ሰባት ጨዋታዎች ሽንፈት አልባ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኙት መቻሎች ከውጤቱም ባሻገር መልካም የሚባል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በተለይም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ማስቆጠር የቻለው የማጥቃት አጨዋወታቸው ለቡድኑ ውጤት ማማር ትልቅ ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። ሆኖም በነገው ጨዋታ ባለፉት ሦስት መርሐብሮች ግብ ካላተናገደው የቅዱስ ጊዮርጊስ የመከላከል አደረጃጀት ቀላል ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ አይገመትም።
በአስራ አንድ ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደረጃቸውን ለማሻሻል የሊጉን መሪ ይገጥማሉ።
ከቅርብ ሳምንታት በኃላ መነቃቃት እየታየበት ያለው የፈረሰኞቹ ስብስብ ላለፉት አራት ጨዋታዎች ሽንፈት አልቀመሰም። በተጠቀሱት መርሐግብሮች ሁለት የድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ቡድኑ የመከላከል አደረጃጀቱ ዋነኛ ጠንካራ ጎኑ ነው። ቡድኑ መረቡን ካስደፈረ ሦስት ጨዋታዎች ከማስቆጠሩም በተጨማሪ ጥቃቶችንም መቀነስ ችሏል። ቡድኑ ግቦችን እያስቆጠረ ከዘለቀው እና ውጤታማ የፊት መስመር ጥምረት ካለው ቡድን ጋር በሚያደርገው ጨዋታ በመከላከሉ ረገድ ላይ ያለውን ጥንካሬ ይዞ መቀጠሉ ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ እንዲወጣ ይረዳዋል ተብሎ የሚገመት ቢሆንም የፊት መስመሩን ውጤማነት ከፍ ማድረግ ይኖርበታል።
ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ ተጋጣሚው በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ እና የተረጋጋ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን እንደመሆኑ በላቀ የአፈፃፀም ብቃት ጨዋታውን መከወን ግድ ይለዋል።
መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ 34 ጊዜ ሲገናኙ 36 ግቦችን ያስቆጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ 12 ጊዜ ድል ሲያደርግ 18 ግቦች ያሉት መቻል ደግሞ 3 ጊዜ አሸንፏል። ቡድኖቹ 19 ጊዜ ነጥብ የመጋራት ታሪክም አላቸው።