ሪፖርት | ድሬዳዋ ሦስት ነጥብን ከሲዳማ ቡና ላይ ወስዷል

አራት ጎሎች በተቆጠሩበት የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ 3ለ1 በሆነ ውጤት ሲዳማ ቡናን ረቷል።

ድሬዳዋ ከተማ ያለ ጎል ካጠናቀቀው የኤሌክትሪክ ጨዋታ ሙኸዲን ሙሳን በመስዑድ መሐመድ በብቸኘነት ያደረጉት ለውጣቸው ሲሆን በፋሲል ከነማ 1ለ0 ተሸንፈው የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ በዛብህ መለዮ እና አስቻለው ሙሴን አሳርፈው ብርሀኑ በቀለ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን እና ይገዙ ቦጋለን በቋሚ አሰላለፍ አካተው ገብተዋል።


የድሬዳዋ ከተማ ብልጫን ከጅምሩ ያሳየን ጨዋታ ጎል የተቆጠረበት በጊዜ ነበር። 4ኛው ደቂቃ ከያሬድ ባዬ ኳስን የተቀበለው ጊትጋት ኩት ቻርለስ ሙሴጌ ጫና ውስጥ ከቶት የነጠቀውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ የግብ ዘቡ ቶማስ ኢካራን መውጣት ተመልክቶ ከፍ በማድረግ ኳሷን መረብ ላይ በማስቀመጥ ብርቱካናማዎቹን ቀዳሚ አድርጓል።

ብልጫውን ወስደው ፈጣን በሆኑ ሽግግሮች የሲዳማ ቡና ሜዳ ላይ ደጋግመው የሚታዩት ድሬዳዋ ከተማዎች እንደነበራቸው የበላይነት አከታትለው ጥቃቶችን ሰንዝረዋል።

በፈጣን መልሶ ማጥቃት አብዱሰላም የሱፍ ወደ ውስጥ ያሻገረውን መሐመድ ኑርናስር በግንባር ገጭቶ በተከላካዮች ተጨርፋ ወጥታበለች። በእንቅስቃሴ ወጥነት አይታይባቸው እንጂ በመስመሮች በኩል መንቀሳቀስን የመረጡት ሲዳማ ቡናዎች በመከላከሉ የነበራቸው ድክመት በተጋጣሚያቸው የሽግግር ጨዋታ ሲጋለጥ የታየ ሲሆን ይገዙ ቦጋለን በጉዳት በደስታ ዮሐንስ መቀየራቸው ደግሞ ማጥቃታቸው ላይ ሌላ ውስንነቶች እንዲኖር ዳርጓል።

እንደ ሲዳማ ቡና ሁሉ ተከላካዩ መሐመድ አብዱልጋኒዮን በጉዳት በድልአዲስ ገብሬ ቀይረው በማጥቃት የበረቱት ድሬዎች 29ኛው ደቂቃ ላይ ቻርለስ ሙሴጌ ያቀበለውን ኳስ ከግራ ሳጥን ውስጥ ያገኘው መሐመድኑር ናስር ከጠባብ አንግል ቶማስ ኢካራ መረብ ላይ ሁለተኛዋን ጎል አክሏል።

ሀብታሙ ታደሠ ከግቡ ትይዩ አግኝቶ ካልተጠቀማት አጋጣሚ በስተቀር የማጥቃት አቅማቸው ተቀዛቅዞ የተስተዋሉት ሲዳማ ቡናዎች ይባስ ብሎ 37ኛው ደቂቃ ላይ ጊትጋት ኩት ቻርለስ ሙሴጌ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የሁለት ፣ የሁለት  ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። ድሬዳዋ ከተማ መስዑድ እና ቻርለስን በሲያም እና ሱራፌል ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው ሬድዋን እና ፍቅረየሱስን በደግፌ እና ኢማኑኤል ላርዬ ተክተዋል።

ከመጀመሪያው አንፃር ወረድ ያለ አጀማመር የተስተዋለበት ሁለተኛው አጋማሽ 48ኛው ደቂቃ ላይ ብርቱካናማዎቹ የግብ መጠናቸውን ወደ ሦስት ከፍ ያደረገች ግብን ሲያገኙ ከቀኝ የተነሳው ማጥቃት መሐመድ ኑርናስር ወደ ሳጥን እየነዳ ገብቶ በድንቅ አጨራረስ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛዋን ጎል አስቆጥሯል።

መሐመድ ኑርናስርን በጉዳት 64ኛው ደቂቃ ላይ ለመቀየር ከተገደዱ በኋላ መጠነኛ መቀዛቀዝ ማጥቃቱ ላይ ያሳዩት ድሬዎች በይበልጥ ጥንቃቄን መርጠው ተንቀሳቅሰዋል።

በአጋማሹ የመጨረሻ ሀያዎቹን ደቂቃዎች ተሻሽለው ቢቀርቡም አብዛኞቹ ኳሶቻቸውን የሚባክኑባቸው ሲዳማዎቹ 70ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ታደሠ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ያደረጋት እና የግቡ አግዳሚ ብረትን ለትማ የተመለሰችው አጋጣሚ የቡድኑ አደገኛ ሙከራ ስትሆን 83ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ሲደርስ ማይክል ኪፕሮፕ ከአህመድ ረሺድ ጋር ታግሎ ኳሷ በሀብታሙ ተጨርፋ አበባየሁ ሀጂሶ ጎል ማድረጉን ተከትሎ ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ የ3ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።