ሪፖርት | በጎል ፌሽታ የደመቀው ጨዋታ በመቻል አሸናፊነት ተቋጭቷል

በማራኪ እንቅስቃሴዎች ታጅቦ ሰባት ጎሎች የተቆጠሩበት የመቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በጦሩ የ4ለ3 ድል አድራጊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

መቻል አርባምንጭ ከተማ ላይ ድል ካስመዘገበው ቡድን ዳንኤል ዳርጌን በአብዱልከሪም ወርቁ በብቸኝነት ለውጥ ሲያደርጉ አራፊ ከመሆናቸው በፊት ከሲዳማ ቡና ጋር ያለ ጎል ባጠናቀቁበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚያቸው ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ፉዓድ አብደላን በአብዱ ሳሚዮ ፣ ተገኑ ተሾመን በቢኒያም ፍቅሬ ቀይረው ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።


በኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው እየተመራ በጀመረው ጨዋታ መቻሎች በሽመልስ በቀለ በጨዋታው ጅማሮ አደገኛ ሙከራ ቢያደርጉም ቀዳሚዋን ጎል ግን ያስቆጠሩት ግን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ናቸው።

2ኛው ደቂቃ ሻሂዱ ሙስጠፋ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ያሻገረውን ኳስ ከተከላካዩ ፍሪምፓንግ ሜንሱ ጋር ታግሎ ኳሷን ያገኘው አማኑኤል ኤርቦ በድንቅ አጨራረስ አልዌንዚ ናፊያን መረብ ላይ አስቆጥሯታል።

መቻሎች በኳስ ንክኪም ይሁን ሜዳውን አስፍተው በመንቀሳቀስ ብልጫውን መያዝ ቢችሉም በመከላከሉ ላይ በነበራቸው ድክመት ግን ሁለተኛዋን ጎል እንዲያስተናግዱ ግድ ብሏቸዋል።

11ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ጥላሁን ከሳጥን ጠርዝ የመታት ኳስ ተከላካዩ ፍሪምፓንግ ለሁለተኛ ጊዜ በጨዋታው በሠራው ስህተት የመጨረሻዋን ኳስ ሳጥን ውስጥ ያገኘው ቢኒያም ፍቅሬ አክርሮ መቶ ተጨማሪ ጎል አድርጓታል።

ሁለት ጎሎችን ካስቆጠሩ በኋላ የተጋጣሚያቸውን ጫና መቋቋም የከበዳቸው ፈረሰኞቹ በርካታ ጥቃቶችን ቢያስተናግዱም የግብ ዘባቸው ባሕሩ ነጋሽ ድንቅ ብቃት መሪነታቸውን አዝልቆላቸዋል።

በሽመልስ በቀለ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተራቸውን የቀጠሉት መቻሎች 38ኛው ደቂቃ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ 41ኛው ደቂቃ ላይ በማስቆጠር ጨዋታውን ወደ 2ለ1 አሸጋግሯል።

በብዙ መልኩ አጋማሹን በተሻለ መንገድ የቋጩት መቻሎች 44ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ጎልን አክለዋል ፤ በረከት ደስታ ከግራ ያገኘውን ኳስ ወደ ውስጥ ጠለቅ ብሎ ይዞ በመግባት ከርቀት እጅግ ግሩም ጎልን ባሕሩ ነጋሽ ላይ በማስቆጠር ጨዋታው 2ለ2 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመራ አስችሏል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ጎል በማስቆጠሩ ፈረሰኞቹ ቀዳሚ ነበሩ። 48ኛው ደቂቃ ላይ ከአማካይ ክፍሉ በረጅሙ ወደ ሳጥን የተላከ ኳስን አማኑኤል ኤርቦ ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርግ በግብ ጠባቂው አሊዮንዚ ናፊያን ጥፋት ተሠርቶበት የተሰጠን የፍፁም ቅጣት ምት ፍጹም ጥላሁን ወደ ጎልነት ለውጧታል።

በጎሎች ታጅቦ የቀጠለው ጨዋታ መቻሎች በፈጣን የሽግግር ጨዋታ በወሰዱት ብልጫ በ52ኛው ደቂቃ አቻ መሆን ችለዋል ፤ በረከት ደስታ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከግራ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ሽመልስ በቀለ በግንባር ገጭቶ የአቻነት ጎሏን አስገኝቷል።

እጅግ ግለቱ ከፍ ብሎ ሳቢነቱ ሳይደበዝዝ የመቻሎች አንጻራዊ የበላይነት ያስተዋልንባቸው ቀጣዮቹ ደቂቃዎች 57ኛው ደቂቃ ላይ ሰባተኛዋን ጎል በጨዋታው ተመልክተናል።

ሽመልስ በቀለ ሳጥን አካባቢ ከተገኘ ቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ የባሕሩ ነጋሽ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት ፍሪምፓንግ ሜንሱ በግንባር በመግጨት የቀድሞ ቡድኑ ላይ አስቆጥሯል።

በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክርን በተመለከትንበት ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ግብን ለማስቆጠር በረጃጅም ኳሶች እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ጨዋታው ግን በመቻሎች የ4ለ3 አሸናፊነት ተደምድሟል ፤ ውጤቱን ተከትሎ ጦሩ የሊግ መሪነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።