ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ጎሎች አርባምንጭ ከተማን 2ለ0 በመርታት ወደ ድል ተመልሰዋል።
ቡናማዎቹ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በአዳማ ሽንፈት ካስተናገደው ቡድን ይታገሱ ታሪኩ እና ሚኪያስ ፀጋዬን በኤርሚያስ ሹምበዛ እና ስንታየሁ ዋለጬ ሲተኩ በመቻል በተመሳሳይ ተሸንፈው የነበሩት አርባምንጮች አሸናፊ ተገኝን በሙሉጌታ ካሳሁን ብቸኛ ቅያሪያቸው አድርገው ገብተዋል።
ግለት አልባ እንቅስቃሴዎችን ከጅምሩ ማስመልከቱን የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና መጠነኛ ማጥቃት በስተቀር አሰልቺነቱ ጉልህ ነበር። በ9ኛው ደቂቃ ዋሳዋ ጄኦፍሪ ከቀኝ ሳጥን በኩል ከቅጣት አሻምቶ ኮንኮኒ ሃፍዝ በግብ ዘቡ ፋሪስ በተያዘበት አጋጣሚ ሙከራ ያደረጉት ቡናማዎች በይበልጥ በቅብብል ከመስመር ወደ ውስጥ በሚጣሉ ኳሶች ጎልን ለማስቆጠር ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ደጋግመው የደረሱ ቢሆንም ይከሰቱ በነበሩ የኃይል አጨዋወቶች በአመዛኙ ጨዋታው ላይ መቀዛቀዞች እንዲኖሩት ዳርጓል። በረጃጅም ኳሶች ለመጫወት ቢዳዱም በቁጥር ማጥቃቱ ላይ አንሰው የሚታዩት አዞዎቹ በተቃራኒው በኢትዮጵያ ቡና በጥቂቱም ቢሆን ተፈትነዋል።
ዲቫይን ዋቹኩዋ ያቀበለውን ወልደአማኑኤል ጌቱ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ደርሶት ወደ ግብ ሞክሮ ፋሪስ ያወጣበት እና ከደቂቃ በኋላም ወልደአማኑኤል ተመሳሳይ ሙከራን ሰንዝሮ በፋሪስ ዳግሞ የመከነበት አጋጣሚ በኢትዮጵያ ቡና በኩል የታዩ ጠጣር ሙከራዎች ነበሩ። ጨዋታው ሊገባደድ በተሰጠው ጭማሪ ላይ አህመድ ሁሴን በረጅሙ የተሰጠውን ኳስ ከተከላካዮች መሐል ሾልኮ ካደረጋት እና በኢብራሂም ዳላንድ ከተያዘችው ብቸኛ የቡድኑ ሙከራ በስተቀር አዞዎቹ ተጨማሪ ጥቃት ሳይሰነዝሩ ቀርተዋል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ኢትዮጵያ ቡና የመሪነት ግባቸውን በጊዜ አግኝተዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ከግራ የተነሳው አንተነህ ተፈራ እየገፋ ይዞ የሄደውን ኳስ መሬት ለመሬት ወደ ውስጥ ሲያሻግር የቡድን አጋሩ ኮንኮኒ ሀፊዝ ያመለጠችውን አጋጣሚ ዲቫይን ዋቹኩዋ ወደ ጎልነት በመለወጥ ቡናማዎቹን ቀዳሚ አድርጓል። የቡና የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን እያስመለከተን የተጓዘው ቀጣዩ ደቂቃ በይበልጥ በመስመሮች በኩል ቡድኑ ማጥቃትን መርጦ ሲንቀሳቀስ አርባምንጮች በአንፃሩ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ሳጥን በመጣል ምርጫቸው በማድረግ ተጫውተዋል።
በጎል ሙከራዎች አይታጀብ እንጂ የኢትዮጵያ ቡና መልሶ ማጥቃት ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርስ ግን አደገኛ ነበር ለዚህም ማሳያው ከዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ ማዕዘን ምት የተቀየረች ኳስን ዲቫይን አሻምቶ ኦካይ ጁል በግንባር በመግጨት ፋሪስ ዕላዊ መረብ ላይ በማሳረፍ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጓል። ተቀራራቢ እንቅስቃሴን ነገር ግን ብዙም የጎል ሙከራዎችን በመጨረሻው አስር ደቂቃዎች ውስጥ በጨዋታው መመልከት ሳንችል በኢትዮጵያ ቡና የ2ለ0 አሸናፊነት በመጨረሻም ተቋጭቷል።