ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

እጅግ ውብ እግር ኳስን ያስመለከተን የባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ በጣና ሞገዶቹ 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባህር ዳሮች ከመቐለው አቻ በሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን አድርገው ፍሬዘር ካሳን በመሳይ አገኘሁ ፣ ፀጋዬ አበራን በጄሮም ፊሊፕ ሲተኩ ከመድን ጋር አቻ በተለያዩት ንግድ ባንኮች በኩል የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ ሲደረግ ተስፋዬ ታምራት ፣ አብዱልከሪም መሐመድ እና ፉዓድ ፈረጃ ወጥተው ብሩክ እንዳለ ፣ ተመስገን ተስፋዬ እና ኤፍሬም ታምራትን በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።

በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደጻድቅ እየተመራ በጀመረው የምሽቱ መርሐግብር በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ተመጣጣኝ አቀራረብ ቢኖረውም በመስመር በኩል በይበልጥ በድግግሞሽ መድረስ የቻሉት ባህር ዳሮች ግን ጎል አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። 10ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ ቸርነት ጠለቅ ብሎ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ፍሬው ሠለሞን ተረጋግቶ በመቆጣጠር መረቡ ላይ አሳርፏታል። ሳቢነቱ ከፍ እያለ በይበልጥ ፈጣን ሽግግሮችን እያሳየን በቀጠለው ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ ሦስቱን የማጥቃት መነሻ ቦታዎች በመጠቀም ለንግድ ባንክ ፈተና የሆኑ ጥቃቶችን አከታትለው ሰንዝረዋል።

አዲስ ግደይ 16ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ካደረጋት እና የግብ ዘቡ ፔፔ ሰይዶ ከያዛት አጋጣሚ ውጪ በቀላሉ የባህር ዳርን የኋላ አጥር ማለፍ የከበዳቸው ሀምራዊ ለባሾቹ በተቃራኒው የተጋጣሚያቸውን ጫና ደግሞ መቋቋም ላይ ደካሞች ነበሩ። በ18ኛው ደቂቃ ፍሬው ጌታሁን በሳጥን ውስጥ ወንድወሰን በለጠ ላይ በሠራው ጥፋት የተገኘን የፍፁም ቅጣት ምት ቸርነት ቢመታው ፍሬው የራሱን ስህተት ኳሷን በማዳን ማረም ችሏል።

 

ግለቱ ከፍ እያለ 36ኛው ደቂቃ ላይ የደረሰው ጨዋታ የባህር ዳርን መሪነት ማሳደግ የቻለች ግብን ሲያስመለክተን ወንድወሰን ከሳጥን ውስጥ አሻምቶ ቸርነት ገጭቶ የመለሳትን ኳስ ጄሮም ፊሊፕ ወደ ጎልነት ቀይሯታል። ከሁለተኛዋ ጎል ከደቂቃ በኋላም ቸርነት ጉግሳ ሌላ ያለቀላት ዕድልን አግኝቶ በተከላካዮች ርብርብ ወደ ውጪ ልትወጣበት ችላለች።

በሁለተኛው አጋማሽ የተመለሰው ጨዋታ ሳቢ በሆነ እንቅስቃሴ የደመቀ ሲሆን ቡድኖቹ ተመሳሳይ አጀማመርን ያድርጉ እንጂ የባህር ዳር ከተማ ስልነት ግን ከቆመበት ቀስ በቀስ የቀጠለ ነበር። ከአማካይ ክፍሉ ከሚመነጩ ኳሶች ሁለቱም መስመሮች በፈጣን ሽግግር በጥልቀት በመጠቀም ለንግድ ባንክ ተከላካዮች ራስ ምታት የሆኑት ባህር ዳሮች በተደጋጋሚ ሳጥን አካባቢ በመድረስ ከፈጠሩት ጫናዎች በኋላ በ75ኛው ደቂቃ ሦስተኛ ጎላቸውን ማግኘት ችለዋል። አብዱልከሪም እና ፈቱዲን ኳስን ወደ ግብ ክልል ይዞ በገባው ጄሮም ፊሊፕ ላይ በሠሩት ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሙጂብ ቃሲም ከግብ ዘቡ ፍሬው ጀርባ ያለው መረብ ላይ ኳሷን አስቀምጧታል።


በሙከራዎች አይድመቅ እንጂ ቶሎ ቶሎ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚደርሱ ኳሶች የተበራከቱበት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ማድረጉ ባይለያቸውም የባህር ዳርን የመከላከል ውቅር ማፍረሱ ላይ የስልነት ችግሮች ነበረባቸው። 87ኛው ደቂቃ ላይ በባህር ዳር በኩል ሄኖክ ይበልጣል ከሳጥን ውጪ አደገኛ ሙከራን ሰንዝሮ የግቡ የላይኛው ብረትን ኳሷ ለትማ ከተመለሰች በኋላ ጨዋታው ተጨማሪ ጎል ሳያስመለክተን በጣና ሞገዶቹ 3ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል።