መረጃዎች | 39ኛ የጨዋታ ቀን

ጉዟቸውን ለማቃናት ድሎችን ማስመዝገብ የሚጠበቅባቸው ከሰንጠረዡ አጋማሽ በታች የተቀመጡትን ክለቦች የሚያገናኙትን የነገ ተጠባቂ መርሐግብሮች እንደሚከተለው ዳስሰናቸዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ወደ ሜዳ የሚገቡት
ሀዋሳ እና መቐለ የሚገናኙበት ጨዋታ የአንዳቸውን የሊግ ጉዞ የማቃናት ዕድልን ይዞ ነገን ይጠብቃል።

በስምንት ነጥቦች ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ኃይቆቹ የደረጃ መሻሻል ለማግኘት ለአራት መርሐግብሮች ከራቃቸው ድል ጋር መታረቅ ግድ ይላቸዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች ምንም እንኳን ባለፉት አራት መርሐግብሮች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች አንዱን ብቻ በማሳካት በነጥብ ረገድ ደካማ ውጤት ማስመዝገብ ቢችሉም ከተከታታይ ሽንፈቶች ካገኙት አንድ ነጥብ በተጨማሪ ከውጤት ባሻገር ብዙ መልካም ነገሮችን አግኝተዋል። በተለይም ቡድኑ ላይ የታየው የአሸናፊነት መንፈስ እና ትጋት ለነገው ጨዋታ ግብአት የሚሆን ነው። በተናጠል ካየነውም የዮሴፍ ታረቀኝ አስተዋጽኦ ከፍ ማለት የቡድኑ የማጥቃት ክፍል አሻሽሎታል። ሆኖም ከወዲሁ አራት ሽንፈቶች ያስተናገዱት እና በጨዋታ በአማካይ አንድ ነጥብ ብቻ ይዘው በመውጣት ላይ የሚገኙት ኃይቆቹ ከሽንፈቶች ተላቀው ቶሎ ወደ ድል መንገድ ካልገቡ ችግር ላይ መውደቃቸው የሚቀር አይመስልም።

በዘጠኝ ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በመጨረሻው መርሐግብር ላይ በተጨማሪ ደቂቃ ባስተናገዱት ግብ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት የተገደዱት መቐለዎች ከሁለት ጨዋታዎች መልስ አንድ ነጥብ ማስመዝገባቸው እንዲሁም ወደ ግብ ማስቆጠሩ መመለሳቸው እንደ አንድ ጥሩ ጎን የሚነሳላቸው ነጥብ ቢሆንም ለሳምንታት ከድል ጋር መራራቃቸው ከሰንጠረዡ አጋማሽ እንዲንሸራተቱ አድርጓቸዋል። ምዓም አናብስት በሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ካስተናገዱ ወዲህ ባደረጉት ጨዋታ ከሌላው ጊዜ የተሻለ የመከላከል አቅም ነበራቸው። ከሌለው የትግራይ ተወካይ ወልዋሎ እና ወላይታ ድቻ በጋራ በርካታ ግቦች በማስተናገድ የሚመሩት መቐለዎች በቀጣይ ቡድኑን ውድ ዋጋ የሚያስከፍሉ የኃላ ክፍል ስህተቶችን የማስተካከል  የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።

ከዚህ ውጪ በጠንካራው የባህር ዳር ከተማ የኋላ ክፍል አንድ ግብ ማስቆጠር የቻለው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት እስከ አምስተኛው ሳምንት ላይ በነበረበት የመልሶ ማጥቃት ጥራት ላይ አይገኝም፤ አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ከላይ ለተጠቀሱት ክፍተቶች መፍትሔ ከማበጀት በተጨማሪ ቡድኑ ካስቆጠራቸው ሰባት ግቦች አምስቱን በማስቆጠር ኃላፊነቱን ለብቻው ከተሸከመው ያሬድ ብርሃኑ በተጨማሪ ኃላፊነቱን ለሌሎች ተሰላፊዎች ጭምር ማካፈል ይኖርባቸል።

 

በሀዋሳ ከተማ በኩል እስራኤል እሸቱ ከመጠነኛ ጉዳት ሲመለስ እንየው ካሳሁን ግን በቅጣት ምክንያት በጨዋታው አይሳተፍም። በመቐለ 70 እንደርታዎች በኩል ያሬድ ብርሃኑ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እና ቤንጃሚን አፉቲ ከጉዳት ማገገም ቢችሉም ዘለግ ላሉ ሳምንታት ቡድናቸው ማገልገል ያልቻሉት የመሃል ተከላካዮቹ መናፍ ዐወል እና ዮናስ ግርማይ እንዲሁም አሸናፊ ሀፍቱ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

 

ቡድኖቹ ኦኪኪ ኦፎላቢ ሀትሪክ በሠራበትና በመቐለ አምስት ለአንድ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው  የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ ውጭ በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው መቐለ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሀዋሳ አንድ  አሸንፏል፤ አንሢ ጨዋታ ደሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር።

ፋሲል ከነማ ከ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ 

በመጨረሻው ሳምንት ትልቅ እፎይታ የሰጣቸውን ድል ያገኙት ዐፄዎቹ የውድድር ዘመኑን ዐይን ገላጭ የሆነ ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ ከሚገቡት ቢጫዎቹ የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ነው።

 

በ11 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በብዙ መልኩ መሻሻል ዐሳይተው ከሳምንታት በኋላ ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ቡድኑ በእርግጥ በንፅፅር ቀለል ከሚል ተጋጣሚ ጋር የሚገናኝ እንደ መሆኑ ከሌላው ጊዜ በተሻለ አጥቅቶ ለመጫወት እንደሚሞክር የሚጠበቅ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በአመርቂ የውህደት ደረጃ ላይ መገኘት ያልቻለው የፊት መስመሩ ጥምረት ግን አሁንም አሰልጣኝ ውበቱ አባተን የሚያሳስብ ጉዳይ ነው። ቡድኑ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ አሁንም ውስንነት ቢኖርበትም የጌታነህ ከበደ መመለስ ግን ለማጥቃቱ የጨመረው ነገር ስለመኖሩ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች እየተመለከትን እንገኛለን።  አጥቂው ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በሦስት ግቦች ተሳትፎ የነበረው ሲሆን በነገው ዕለትም ጨዋታውን በቋሚነት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

 

ብቸኛው ነጥብ ያላስመዘገበው የሊግ ክለብ የሆነው ወልዋሎ ከአስከፊው አጀማመር ለመውጣት እንዲሁም ከወዲሁ እየሰፋ የሚገኘውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ድል አስፈላጊው ነው።

በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ወልዋሎዎች በአዲሱ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እየተመሩ ባከናወኑት ጨዋታም ሽንፈት ማስተናገድ ቢችሉም መጠነኛ መነቃቃት ዐሳይተዋል። ቡድኑ የፈለገውን ውጤት ባያሳካም በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የሚታይ መሻሻል ዐሳይቷል። ነገም ደካማ አጀማመሩን ከማቅናት ባለፈ ለቀጣይ መርሐግብሮች የሚሆን የስነ ልቦና ስንቅ የሚሸምትበት አልያም የውጤት እጦቱን የሚያባብስበትን የሞት ሽረት ጨዋታ የሚያደርግ ይሆናል።

በብዙ መመዘኛዎች በቂ በሚባል ደረጃ ላይ የማይገኘው ቡድኑ በአሁናዊ የሰንጠረዡ አቀማመጥ መሰረት 14ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው በ9 ነጥብ ርቆ ይገኛል፤ በመሆኑም ይህን ርቀት ለማጥበብ ከወዲሁ ነጥብ መሰብሰብ ግድ ይለዋል።

በፋሲል ከነማ በኩል አፍቅሮተ ሰለሞን በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን የአቤል እንዳለ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። በወልዋሎ በኩል ሳምሶን ጥላሁን እና ናትናኤል ዘለቀ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ አምበሉ በረከት አማረም በቅጣት ምክንያት በጨዋታው አይሳተፍም።

ቡድኖቹ የተሰረዘው እና በፋሲል ከነማ 1ለ0 አሸናፊነት የተጠናቀቀው የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይተው ወልዋሎ ምንም አላሸነፈም።