ሪፖርት | በሙከራዎች ታጅቦ የተካሄደው ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል

የሀይቆቹ ፊታ አውራሪ ዓሊ ሱሌይማን እና የምዓም አናብስቱ የግብ ዘብ ሶፎንያስ ሰይፈ ደምቀው የዋሉበት ጨዋታ በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ሀዋሳ ከተማዎች ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ አሰላለፍ ፈቃደስላሴ ደሳለኝ በሰለሞን ወዴሳ ተክተው ሲገቡ መቐለ 70 እንደርታዎች በበኩላቸው ከባህርዳር ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ ሔኖክ አንጃው እና ተመስገን በጅሮንድ በቤንጀሚን ኮቴ እና ያሬድ ብርሀኑ ተክተው ገብተዋል።

በሁሉም ረገድ ተቀራራቢ የሚባል ፉክክር የታየበት እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረገበት የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የማጥቃት ፍላጎት ቢስተዋልም ወደ ሙከራነት የተቀየሩት ግን ጥቂቶቹ ነበሩ። በአጋማሹ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በመድረስ የተሻሉ በነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በኩል ዐሊ ሱሌይማን ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ሶፎንያስ ሰይፈ በጥሩ መንገድ ግብ ከመሆን የመለሳት ኳስ እንዲሁም በተመሳሳይ አጥቂው ዐሊ ሱሌይማን ከመሀል ሜዳ እየገፋ ወደ ሳጥኑ ይዟት ገብቶ መቷት የግቡን ቋሚ የመለሳት ኳስ ሀይቆቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ደግሞ ሰለሞን ሀብቴ ከተከላካዮች በረዥሙ የተሻገረችውን ኳስ በአግባቡ ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ሳጥን አሻምቷት በግቡ አፋፍ ያሬድ ብርሀኑ ወደ ግብነት ያልቀየራት ኳስ ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ወርቃማ ዕድል ነበረች።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ የታየበት እና የሀዋሳ ከተማዎች ሙሉ ብልጫ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሀይቆቹ በርከት ያሉ ሙከራዎች ያመከኑበት ነበር።


ከአጋማሹ የመጀመርያ ደቂቃዎች ጀምሮ በጥሩ የማጥቃት ፍላጎት የጀመሩት ሀይቆቹ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ዮሴፍ ታረቀኝ በጥሩ መንገድ ከመስመር አሻግሯት ዓሊ ሱሌይማን ግብ ጠባቂውን ጭምር አልፎ ወደ ግብነት ያልቀየራት ኳስ፤ ዮሴፍ ታረቀኝ ተቀይሮ የገባው አቤኔዘር ዮሐንስ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም ዓሊ ሱሌይማን ከታፈሰ ሰለሞን በግሩም መንገድ የተሻገረችለትን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ መቷት ሶፎንያስ ሰይፈ በምያስደንቅ ብቃት ያዳናት እና በጨዋታው ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ዓሊ ሱሌይማን በሳጥኑ ውስጥ አክርሮ መቷት የግቡን አግዳሚ ለትማ የተመለሰች ኳስ ሀይቆቹን አሸናፊ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። በአጋማሹ በመከላከል ላይ ተጠምደው የዋሉት መቐለዎችም አልፎ አልፎ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ማግኘት ቢችሉም ሰለሞን ሀብቴ ከመሀል ሜዳ ተጫዋቾች እየቀነሰ ወደ ሳጥን ገብቶ መቷት ሰይድ ሀብታሙ ከመለሳት ኳስ ውጭ ይህ ነው የሚባል የጠራ ዕድል ሳይፈጥሩ ጨዋታው ተጠናቋል።