መረጃዎች | 40ኛ የጨዋታ ቀን

የ10ኛው ሳምንት ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይገባደዳል፤ መርሐግብሮቹን አስመልክተን ያዘጋጀናቸውን መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።

ስሑል ሽረ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በደረጃ ሰንጠረዡ የተለያየ ክፍል የሚገኙ ክለቦች ወደ ድል ለመመለስ የሚደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

ከመጀመርያው ሳምንት ድል በኋላ ላለፉት ሰባት መርሐግብሮች ማሸነፍ ያልቻሉት ስሑል ሽረዎች በሰባት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን በጉዳት፣ በግል ጉዳዮች እና በህመም ሙሉ ስብስባቸው ባላገኙባቸው ያለፉት መርሐግብሮች በብዙ ረገድ የተዳከመ ብቃት በማሳየት በሂደት የመከላከል ጥንካሬያቸውን እያጡ ይገኛሉ። በውድድር ዓመቱ በጨዋታ በአማካይ 1.1 ግብ ካስተናገደው የቡድኑ የመከላከል ጥምረት በተጨማሪ ግቦችን በሚፈለገው መጠን ማምረት ያልቻለው እና በሊጉ ጥቂት ግቦችን በማስቆጠር ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የፊት መስመሩም ቢሆን ቡድኑ ለሳምንታት ከድል ጋር እንዲራራቅ ምክንያት ሆኗል።

አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በቀጣይ በመጀመርያው ጨዋታ አዳማ ከተማ ላይ ሦስት ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ በተቀሩት ሰባት ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን ብቻ ማስቆጠር የቻለውን በደካማ የውጤታማነት ደረጃ የሚገኘው የፊት መስመሩ ጥምረት ላይ ማስተካከያዎች ማድረግ ግድ ይለዋል። በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ስሑል ሽረ ከአደጋው በመጠኑ ፈቀቅ ለማለት ባነገው ጨዋታ ሙሉ ውጤት ያስፈልገዋል። ቡድኑ ሳይጠበቅ ጥሩ አጀማመር አድርጎ የነበረ ቢሆንም በሂደት ተዳክሞ የነጥብ ድምሩን ማሳደግ ተቸግሮ ደረጃውም አሽቆልቁሏል ፤ በነገው ዕለትም ለሳምንታት ከናፈቀው ድል ጋር ለመገናኘት ጥቂት ሽንፈት የቀመሰውን ጠጣሩን የዘሪሁን ሸንገታ ቡድን ይገጥማል።

ላለፉት ስምንት ሳምንታት ምንም ሽንፈት ያልቀመሱት እና በሊጉ ከመቻል እና ኢትዮጵያ መድን ጋር በጋራ ጥቂት ሽንፈቶች በማስተናገድ በቀዳሚነት የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ድል ለማግኘት ስሑል ሽረን ይገጥማሉ።

የመከላከል አደረጃጀታቸው በርከት ያሉ ጥቃቶች ባስተናገደበት የመጨረሻው ጨዋታ ላይ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ የወጣው ቡድኑ ከተከታታይ የአቻ ውጤት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ያልማል። ኤሌክትሪክ በነገው ዕለት በድሬዳዋው ጨዋታ ካሳየው የበዛ ጥንቃቄ የተሞላበት አቀራረብ በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን እንደወትሮው ለመስመር ተጫዋቾቹ ከፍ ያለ የማጥቃት ኃላፊነት ሰጥቶ እንደሚገባ ይገመታል።

በስሑል ሽረ በኩል ጉዳት ላይ የነበረው አሌክስ ኪታታ ጨምሮ በቤተሰብ ችግር ምክንያት ከቡድኑ ጋር ያልነበረው ኤልያስ አሕመድ እና በወባ ህመም ምክንያት በመጨረሻው ጨዋታ ያልተሳተፈው ነጻነት ገብረመድኅን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆኑ ተከላካዩ ሱሌይማን መሐመድ ግን ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው። በኤሌክትሪክ በኩል ጉዳት አጋጥሞት ባለፈው ተቀይሮ የወጣው ግብ ጠባቂው እንድሪስ እንዲሁም ጉዳት ላይ የሰነበቱት ሀብታሙ ሽዋለም፣ አበባየሁ ዮሐንስ እና አባይነህ ፌኖ ከጉዳታቸው አገግመው ለነገ ጨዋታ የሚደርሱ ሲሆን የረጅም ግዜ ጉዳት ላይ የነበረው ገለታ ኃይሉ ለነገ ጨዋታ ባይደርስም ልምምድ መጀመሩ ታውቋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ይጫወታሉ።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ አዳማ ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ መዝጊያ የሆነው በሁለት ነጥብ የሚበላለጡ ክለቦችን የሚያገናኘውን ጨዋታ አስመልክተን ያዘጋጀናቸው መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።

ሦስት ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ አስራ ሦስት ነጥቦች ሰብስበው 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ነብሮቹ አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበው ወደ መሪዎቹ ጎራ ለመቀላቀል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች መረባቸውን ያላስደፈሩት ነብሮች ወደ የባለፈው ዓመት ዋነኛ ጥንካሬያቸው ተመልሰዋል፤ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው ቡድኑ በመጀመርያዎቹ ሦስት መርሐግብሮች የነበሩበትን ድክመቶች ቀርፎ ወደ ተለመደው ጥንካሬው ተመልሷል። በእርግጥ ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ለውጦች ማምጣቱ ባይካድም አሁንም ለፊት አጥቂዎቹ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ብዙ መሻሻሎችን ይፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ ከተጋጣሚያቸው ስል የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አንፃር ጠጣር አቀራረብ እንዲሁም በተለመደው በመስመሮች እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር የሚሞክር የጨዋታ ዕቅድ ይዘው የሚቀርቡበት ዕድል እንዳለም ይገመታል።

 

ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች መልስ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፈው ወደ ድል የተመለሱት አዳማ ከተማዎች በአስራ አንድ ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ቡድኑ ከሁለት ጨዋታዎች መልስ ወሳኝ ድል ባስመዘገበበት ጨዋታ በብዙ ረገድ ብልጫ ቢወሰድበትም የመረጠው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ውጤታማ አድርጎታል። ለ180′ ደቂቃዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖት የነበረው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ወደ ግብ ማስቆጠር መመለሱም በጨዋታው ከታዩ አወንታዊ ጎኖች አንዱ ነው። አዳማ ከተማዎች አሁን ላይ እየተገበሩ የሚታዩት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ለተጋጣሚ አስቸጋሪ ቢሆንም የአፈፃፀም ውጤታማነቱን ግን ይበልጥ ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።

በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ሄኖክ አርፊጮ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ እና ጫላ ተሺታ ልምምድ ቢጀምሩም በጨዋታው የመሰለፋቸው ጉዳት አልለየለትም ። በአዳማ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ልምምድ ቢጀምርም ከነገው ጨዋታ ውጪ ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ ዳንኤል ደምሱ እና ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ በጉዳት፤ ተከላካዩ ፍቅሩ ዓለማየሁ በቅጣት ምክንያት በጨዋታው አይሳተፉም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 10 ጊዜ ተገናኝተው ሀዲያ ሆሳዕና አራት ጊዜ፤ አዳማ ከተማ ደግሞ ሦስት ጊዜ ሲያሸነፉ ሦስቱ ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። አዳማ 11 ሀዲያ ደግሞ 12 ግቦችን አስቆጥረዋል።