ሪፖርት | ስሑል ሽረ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ስሑል ሽረ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታቸውን ነጥብ በመጋራት ፈጽመዋል።

ስሑል ሽረዎች በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና ከተረታው ስብስብ ባደረጓቸው አራት ለውጦች ጥዑመ ልሳን ኃ/ሚካኤል ፣ ዊልያን ሰለሞን ፣ ብሩክ ሀዱሽ እና አልዓዛር አደማሱ አስወጥተው በምትካቸው ነፃነት ገብረመድህን ፣ ኤልያስ አህመድ ፣ አሌክስ ኪታታ እና ፋሲል አስማማውን ተክተው ሲያስገቡ በአንፃሩ በአንፃሩ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ኤሌክትሪኮች አብዱላሂ አልዩ እና ሄኖክ ገብረሕይወት ወጥተው በምትካቸው በፍቃዱ አስረሳኸኝ እና አበባየሁ ዮሀንስ ተከተው ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።


የኢትዮ ኤሌክትሪኮች የበላይነት በታየበት የመጀመሪያ ደቂቃዎች ኤሌክትሪኮች በ5ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ከተሻማ ኳስ አሸናፊ ጥሩነህ በግንባሩ በመግጨት በሞከራት እና ሞይስ ፖዎቲ በግሩም ሁኔታ ባዳነበት እንዲሁም በ7ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ዓለሙ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ባደረጋት አደገኛ ሙከራ ገና በማለዳው ቀዳሚ ለመሆን ጥረዋል።

በአጋማሹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን ይዘው ለመውሰድ ሲታትሩ የነበሩት ሽረዎች በአመዛኙ የኳስ ቅብብላቸው ከመሀል ሜዳ የዘለለ አልነበረም ፤ በዚህም ይህ ነው የሚባል ጥቃት ለመሰንዘር እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል።

ያለግብ ከተጠናቀቀው አጋማሽ መልስ በተወሰነ መልኩ ወደ ተቃራኒ ሜዳ በተሻለ ለመድረስ ጥረት በማድረግ የጀመሩት ሽረዎች እንደ መጀመሪያው ሁሉ በመጨረሻው ሲሶ የነበራቸው አፈፃፀም ፍፁም ደካማ ነበር።
በአመዛኙ መሀል ሜዳ ላይ ያመዘነው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ በሙከራዎች ረገድ ፍፁም የተዳከመ ነበር ፤ በዚህም በብዙ መመዘኛዎች ደካማ የነበረው ጨዋታ ያለ አሸናፊ በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።